የንስሀ እናት
የንስሀ እናት ከ አሸናፊ አበራ (ጥላ ዘ ፅጌ) ሰውየው የመንፈስ ድርቅ መቶታል፡፡ ፀጉሩ ተንጨፍሯል ፊቱ እንደከረመ ሬሳ ገርጥቷል ከናፍሮቹ እንደ ግብዝ ጾመኛ ከናፍር ክው ብለው ደርቀዋል አይኖቹ በሞትና በከባድ እንቅልፍ መካከል ባለ አንዳች ነገር ተሞግተው ቦዘዋል፡፡ አለባበሱ ተመሰቃቅሏል ሸሚዙ በአንድ ጎን ከሱሪው ወጥቶ ተንከርፏል ከረቫቱ እስከ ደረቱ ላልቶ ተንዘላዝሏል ኮቱን እንደ ነገሩ በእጁ አንጠልጥሎ መሬት ላይ በመጎተት አይነት ይዞታል፡፡ አስተውሎ ለተመለከተው ሰውየው ሞት እና ህይወት ተስፋና ቀቢፀ ተስፋ እምነትና ክህደት መንፈስና ስጋ የየግል ግዛታቸው ለማድረግ ባደረጉት ታላቅ እና የማያባራ ግጭት የተነሳ ባጭር ደስታና በጥልቅ ሀዘን መካከል እንደተዉት ያስታውቃል፡፡ ሚስቱ በረዥም እንቅልፍ አልባ ሌሊት ያልተፈታ ውብ ገላዋን ለጠዋቷ ፀሀይ ሰጥታ በረንዳ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ፀሀይዋ የሴቲቱን ወርቃማ ጸጉር በብርሀንዋ እያለሰለሰች እና በለበሰችው ስስ የሌሊት ልብስ አልፋ ገላዋን በሙቀቷ እየዳበሰች የምሽት ጭንቀቷን ለማስረሳት ትጥራለች፡፡ አዋፍ በበኩላቸው አንዳች የህይወት ሚስጥር በረቂቅ ዜማቸው ለውቢቷ ለመናገር ይለፋሉ ሴቲቱ ግን በጠባቂ ሰው መንፈስ ሁሉን ችላ ብላ በሀሳብ ማዕበል ትናጣለች፡፡ ባሏ የሞት ሞቱን የግቢውን በር ገፍቶ ሲገባ ስታይ ደስታ እና ሀዘን ቁጣ እና እፎይታ በተቀላቀለበት ቅጥ የለሽ ስሜት ተነስታ ተቀበለችው:: ልክ ጫጩቶቻ ከጎጇቸው ያለጊዜ በረው ርቀው ጠፍተው በተአምር እንደተመለሱላት ንስር ወፍ እጆቿን እንደ ክንፍ ዘርግታ የሆዷን ልትመግበው በሚመስል ደግነት አፏን አሞጥሙጣ ተጠጋችው፡፡ ባሏ የሚስቱን የተዘረጉ እጆች እና ከናፍር ችላ ብሎ በጥይት እንደተመታ አይነት ቁልቁል ተምዘግዝጎ እግሯ ስር ተነ...