ልጃገረዷ መቐለ (የጉዞ ማስታወሻ)
ልጃገረዷ መቐለ ( የጉዞ ማስታወሻ) አሸናፊ አበራ ከአላማጣ ጀመሮ ልጃገረዶች በየመንገዱ መኪናችንን ከበው እያስቆሙ የአሸንዳ ዘፈን እየዘፈኑ ይጨፍራሉ፡፡ በሹፌራችን በኩል ገንዘብ ይሰጣቸዋል፣ በእልልታና በሙገሳ መንገዱን ይለቁልንና እንሄዳለን፡፡ እንደገና ያስቆሙናል፡፡ ሸልመን እንሄዳለን፡፡ እንደገና ያስቆሙናል፡፡ ሸልመን እንሄዳለን፡፡ እንዲህ በአሸንዳ ዜማና ጭፈራ ታጀብን ረዥሙ ጉዞ የፈጠረብንን ድካም እረስተን አመሻሹ ላይ መቀሌ ከተማ ገባን፡፡ ….. የሰሜን ኢትዮጵያ ትልቋ ከተማ መቀሌ ፀጉሯን አልባሶ ፣ ግልብጭ፣ጋመ እና ድርብ ተሰርታ፤ ውብ የ ሹፎን፣ የ ጃርሲ፣ የመልጉም እና የ ጥልፍ ቀሚስ ለብሳ፤ እንደ ሕንቆ፣ አልቦ፣ ድሪ፣ ድኮት፣ ጉትቻ፣ ማርዳ፣ መስቀል በመሳሰሉ ልዩ ልዩ ጌጣጌጥና ቁሶች ደምቃ ትኩስና የምታሳሳሳ ልጃገረድ ሴት ሆኗ አገኘናት፡፡ ….. በእጅ ቢነኩ የሚፈርጡ በሚመስሉ እንቡጥ ጽጌሬዳ ልጃገረዶች ውበት ፈዘን ከቆምንበት ስንነቃ አልጋ መፈለግ ጀመርን፡፡ አሸንዳ ከ ነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 18 ቀን ድረስ በመላው ትግራይ የሚከበር በዓል በመሆኑ በዋናዋ የትግራይ ከተማ አልጋ የሚባል ነገር የለም፡፡ ነገ ስራ ባይኖረን ከነዚህ የቁንጅና አድባሮች ጋር እየዞርን ለውበት ቅኔ ስንቀኝና ውዳሴ ስናቀርብ ማህሌት ቆመን በነጋ ብለን ስንፎክር ዳህላክ አካባቢ አልጋ አገኘን፡፡ ….. አሁን ደግሞ እራት የመፈለጊያ ጊዜ ነው፡፡ ቀኑ ሮብ በመሆኑ የጾም ምግብ ፍለጋ ዝናቡን ችለን እግራችን እንደመራን የጾም ምግብ ለማደን ዞርን፡፡ ትግራይ በክሽን ሽሮ አትታማም፣ ለዚህ ደግሞ የትግራይ ስም ይዘው አዲስ አበባን የወረሩት ሽሮ ቤቶች ህያው ምስክሮች ና...