የንስሀ እናት



የንስሀ እናት

አሸናፊ አበራ (ጥላ ዘ ፅጌ)

ሰውየው የመንፈስ ድርቅ መቶታል፡፡ ፀጉሩ ተንጨፍሯል ፊቱ እንደከረመ ሬሳ ገርጥቷል ከናፍሮቹ እንደ ግብዝ ጾመኛ ከናፍር ክው ብለው ደርቀዋል አይኖቹ በሞትና በከባድ እንቅልፍ መካከል ባለ አንዳች ነገር ተሞግተው ቦዘዋል፡፡ አለባበሱ ተመሰቃቅሏል ሸሚዙ በአንድ ጎን ከሱሪው ወጥቶ ተንከርፏል ከረቫቱ እስከ ደረቱ ላልቶ ተንዘላዝሏል ኮቱን እንደ ነገሩ በእጁ አንጠልጥሎ መሬት ላይ በመጎተት አይነት ይዞታል፡፡
አስተውሎ ለተመለከተው ሰውየው ሞት እና ህይወት ተስፋና ቀቢፀ ተስፋ እምነትና ክህደት መንፈስና ስጋ የየግል ግዛታቸው ለማድረግ ባደረጉት ታላቅ እና የማያባራ ግጭት የተነሳ ባጭር ደስታና በጥልቅ ሀዘን መካከል እንደተዉት ያስታውቃል፡፡
ሚስቱ በረዥም እንቅልፍ አልባ ሌሊት ያልተፈታ ውብ ገላዋን ለጠዋቷ ፀሀይ ሰጥታ በረንዳ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ፀሀይዋ የሴቲቱን ወርቃማ ጸጉር በብርሀንዋ እያለሰለሰች እና በለበሰችው ስስ የሌሊት ልብስ አልፋ ገላዋን በሙቀቷ እየዳበሰች የምሽት ጭንቀቷን ለማስረሳት ትጥራለች፡፡ አዋፍ በበኩላቸው አንዳች የህይወት ሚስጥር በረቂቅ ዜማቸው ለውቢቷ ለመናገር ይለፋሉ ሴቲቱ ግን በጠባቂ ሰው መንፈስ ሁሉን ችላ ብላ በሀሳብ ማዕበል ትናጣለች፡፡
ባሏ የሞት ሞቱን የግቢውን በር ገፍቶ ሲገባ ስታይ ደስታ እና ሀዘን ቁጣ እና እፎይታ በተቀላቀለበት ቅጥ የለሽ ስሜት ተነስታ ተቀበለችው:: ልክ ጫጩቶቻ ከጎጇቸው ያለጊዜ በረው ርቀው ጠፍተው በተአምር እንደተመለሱላት ንስር ወፍ እጆቿን እንደ ክንፍ ዘርግታ የሆዷን ልትመግበው በሚመስል ደግነት አፏን አሞጥሙጣ ተጠጋችው፡፡
ባሏ የሚስቱን የተዘረጉ እጆች እና ከናፍር ችላ ብሎ በጥይት እንደተመታ አይነት ቁልቁል ተምዘግዝጎ እግሯ ስር ተነጠፈ፡፡
አንዳች ጉዳት ከሰውነቱ ላይ ለማግኘት እየተርበተበተች መላ አካሉን ዳበሰችው፡፡ እግሯን እንዳቀፈ ህይወት አልባ በሆነ የጣር ድምፅ “በ..ድ..ዬ..ሻለሁ ደጋግሜ ገድዬሻለሁ፡፡ ገላዬን ሰርቄሻለው፡፡ አሁን ግን ድብብቆሹ አቃተኝ ታማኝነትሽ አሳደደኝ፡፡ ንጽህናሽ መንፈሴን የእረፍት ውሃ ከለከላት አልቻልኩም፡፡ ሀጢያቴን የምናዘዝልሽ ይቅር እንድትይኝ አይደለም፡፡ በደሌ ስርየት እንደሌለውም አውቃለው፡፡ ይቅርታ ብታደርጊልኝ እንኳን ይቅርታሽ ጨርሶ ይገለኛል፡፡ ብቻ እወቂ” ብሎ ንግግሩን ሳይቋጨው ቃላት አፉ ውስጥ ሟሙተው ተሰወሩበት፡፡
ሚስቱ ሁሉ ነገር በአንድ ጊዜ ፀጥ ረጭ አለባት፡፡ የልቧ ምት ቆመ፡፡ ደሟ በደም ስሮቿ ውስጥ እረግቶ ተሰነቀረ፡፡ የአፏ ምራቅ በሰውነቷ ትኩሳት ደርቆ ምላሷ መላወስ አቃተው፡፡ ከንፈሯ ከባድ ህመም እንደመታው ሰው ከንፈር ክው ብሎ ደረቀ፡፡ ትላልቅ አይኖቿ ጉድጓዳቸው ውስጥ ተጣብቀው ፈጠው ቀሩ፡፡ መላ አካሏ ጥሩ የስነ ቅርጽ ባለሙያ ፈልፍሎ እንዳቆመው የህይወት ቅጂ ሀውልት ግትር አለባት፡፡
የሞተች መሰላት፡፡ ለአፍታ ይሁን ለዘላለም ለማይተመን ጊዜ በሞትና በህይወት መካከል በተዘረጋው አጭር ድልድይ ላይ ወዲያና ወዲህ ስትመላለስ ቆይታ ልክ በጠንካራ ክንድ አንገቱ ውሃ ውስጥ ተዘፍቆ ቆይቶ እንደተለቀቀ ሰው ረዥም ትንፋሽ ወደ ውስጧ ተንፍሳ ተንፈራግጣ ተመለሰች፡፡
ከዚያም ያለ የሌለ አቅሟን አሰባስባ በተሰበረ ድምጽ ‘’ባሌ እኔም ሚስትህ የምትለኝን ያህል ታማኝ አይደለሁም፡፡ እኔም በድዬሀለው ገላዬን ሰርቄህ ወስልቻለው፡፡ ብቻህን አልበደልክም፡፡ ይልቅስ አንተ ከኔ በላይ ታማኝና መልካም በመሆንህ ነው ይህ ሁሉ ጸጸት የተሰማህ፡፡ እኔ ግን ልበ ደንዳናና ጨካኝ ሴት በመሆኔ በደሌ ተስማምቶኝ እስከዚች ሰዓት ድረስ ደብቄው ኖርኩ፡፡ እባክህ ይቅር በለኝ ይቅር እንባባል እራስህን ከሚገባው በላይ አትቅጣው‘’ ብላ ስርቅታ ጉሮሮዋን ዘጋው፡፡
ባሏ ከደቀ መዛሙርቱና ከህዝቡ መሀል በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተገኝቶ የመሲውን ፍርድ እንደሰማ ሁሉ በሚስቱ ቃል ተጽናና፡፡ በንጉስ ሳኦል እልፍኝ ታድሞ የብላቴናው ዳዊትን መዝሙረ በገና ያጣጣመ ይመስል የተረበሸ መንፈሱ በሚስቱ ቃል ተረጋጋ፡፡
ከተንበረከከበት ተነስቶ ለጥቂት ጊዜ ሚስቱን ትክ ብሎ ሲመለከታት ከቆየ በኋላ ከበፊቱ ፍጹም በተለየ ሁኔታ በፍጥነት ወደ በሩ ተራምዶ መጥቶ ሄደ፡፡
ከቆመችበት ሳትነቃነቅ በእንባ በተሞሉ የአይኖቿ ብዥታ ውስጥ ባሏን ተመለከተችው የጠፋበት አንድያ በጉ እንደተገኝለት እረኛ እራሱን አቅፎ በሀሴት ይራመዳል፡፡ በተራራ አበቦች መሀል እንደሚንሸራሸር ሰው መንፈሱ ተዝናንቷል፡፡ ብቻውን አይደለም፡፡ ብቻውንም አልበደለም፡፡
ግቢውን ጨርሶ ወጥቶ ከአይኗ ሲሰወር ፈጥና ተንበረከከች፡፡ አይኗን ወደ ጠዋቱ ሰማይ አንስታ በሽንፈትና በድል መንፈስ ሀዘንና ደስታ በተጋባበት ድምጽ “አምላኬ ባሌ በጥፋተኝነት እሳት እራሱን ሲለበልብ እኔ በንፅህናዬ የግብዝነት ማማ ላይ ቆሜ ቁልቁል እያየሁት ወደ እራስ መጥላትና ተስፋ መቁረጥ እንዳልመራው ስለረዳህኝ አመሰግንሀለው፡፡ አንተ ሰውን  ከማያባራ ፍላጎት ነው የሰራኸው፡፡ ሰውነት የፍላጎት ባርነት ሲሆን ጽድቅ ማለት ደግሞ ሰው መሆንን ተቀብሎ ፍላጎትን አቀዳድሞ የመኖር ፈተና ነው፡፡
ባሌ ሰው ነው ሰው መሆኑን እንዲያምን ሰው መሆኔን አሳየሁት፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ ያልሰራሁትን ስህተት እንደ ፈጸምኩት ተናዝዤ ሸክሙን ያቀለልኩለት፡፡
ባሌ ለጊዜው በኔ ላይ እምነት ላይኖረው ይችላል እኔን መጠርጠር ሲችል ግን እራሱን መጠርጠር ይማራል፡፡ ያኔ የሚታመን እንደሌለ ሲያውቅ እራሱን ማመን እንደሚችል ይገለጥለታል፡፡ ልክ እራሱን ማመን በጀመረበት ቅጽበት ደግሞ እኔንም ማመን ይችላል፡፡ ባሌ በኔ የተነሳ የሰውን ልጅ ድካም ይቀበላል የሰውን ድካም ሲቀበል ለራሱ ይቅርታ ያደርጋል ለራሱ ይቅርታ ማድረግ ሲችል ደግሞ እኔንም ይቅር ይለኛል፡፡
አንተ ከምንም በላይ ሰው አድርገህ ስለፈጠርከን ከምንም በላይ ሰው ሆነን ኖረን ሰው ሆነን እንድንሞት ትፈልጋለህ” ብላ አንዳች መልስ የምትጠብቅ ይመስል ሰማዩ ላይ ፈዛ ቀረች፡፡
የንጋት ፀሀይና የንጋት ወፍ የሆነውን ሁሉ ባስተዋሉ ጊዜ ሰው የመሆንን ሚስጥር በማወቃቸው ተደነቁ፡፡ ንጋቱ ግን በባሏ ደስታና በሴቲቱ እውነት ግራ ተጋብቶ ፈዞ ደመቀ ደምቆ እንደገና ፈዘዘዘ እንደገናም….

                             ‹አልተፈፀመም›


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ከ “ተደምሬያለው!!” ባሻገር

ውኃ ይሰማል ጉድ በል አበሻ ውኃ ይሰማል አለች ፈረንጅ

ዶ/ር ዐብይ የህመም ማስታገሻ ወይስ መድሀኒት?