ልጃገረዷ መቐለ (የጉዞ ማስታወሻ)

አሸናፊ አበራ
ከአላማጣ ጀመሮ ልጃገረዶች በየመንገዱ መኪናችንን ከበው እያስቆሙ የአሸንዳ
ዘፈን እየዘፈኑ ይጨፍራሉ፡፡ በሹፌራችን በኩል ገንዘብ ይሰጣቸዋል፣ በእልልታና በሙገሳ መንገዱን ይለቁልንና እንሄዳለን፡፡ እንደገና
ያስቆሙናል፡፡ ሸልመን እንሄዳለን፡፡ እንደገና ያስቆሙናል፡፡ ሸልመን እንሄዳለን፡፡ እንዲህ በአሸንዳ ዜማና ጭፈራ ታጀብን ረዥሙ
ጉዞ የፈጠረብንን ድካም እረስተን አመሻሹ ላይ መቀሌ ከተማ ገባን፡፡
…..
የሰሜን ኢትዮጵያ ትልቋ ከተማ መቀሌ ፀጉሯን አልባሶ፣ግልብጭ፣ጋመ እና ድርብ ተሰርታ፤ ውብ የሹፎን፣ የጃርሲ፣ የመልጉም እና የጥልፍ ቀሚስ ለብሳ፤ እንደ ሕንቆ፣ አልቦ፣ ድሪ፣ ድኮት፣ ጉትቻ፣ ማርዳ፣ መስቀል በመሳሰሉ ልዩ ልዩ ጌጣጌጥና ቁሶች ደምቃ ትኩስና የምታሳሳሳ ልጃገረድ ሴት ሆኗ አገኘናት፡፡
…..
በእጅ ቢነኩ የሚፈርጡ
በሚመስሉ እንቡጥ ጽጌሬዳ ልጃገረዶች ውበት ፈዘን ከቆምንበት ስንነቃ አልጋ መፈለግ ጀመርን፡፡ አሸንዳ ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 18 ቀን ድረስ በመላው ትግራይ የሚከበር በዓል በመሆኑ
በዋናዋ የትግራይ ከተማ አልጋ የሚባል ነገር የለም፡፡ ነገ ስራ ባይኖረን ከነዚህ የቁንጅና አድባሮች
ጋር እየዞርን ለውበት ቅኔ ስንቀኝና ውዳሴ ስናቀርብ ማህሌት ቆመን በነጋ ብለን ስንፎክር ዳህላክ አካባቢ አልጋ አገኘን፡፡
…..
አሁን ደግሞ እራት የመፈለጊያ ጊዜ ነው፡፡ ቀኑ ሮብ በመሆኑ የጾም ምግብ
ፍለጋ ዝናቡን ችለን እግራችን እንደመራን የጾም ምግብ ለማደን ዞርን፡፡
ትግራይ በክሽን ሽሮ አትታማም፣ ለዚህ ደግሞ የትግራይ ስም ይዘው አዲስ አበባን የወረሩት ሽሮ ቤቶች ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ ዛሬ
ግን ከተማዋን ባጥለቀለቃት የአሸንዳ እንግዳ ምክንያት አብዛኛው ቤት ምግብ አልቋል፡፡ በአደናችን መሀል የቄራ መኪና ከአንድ ምግብ
ቤት በራፍ ላይ ቆሞ ስጋ ሲያወርድ ተመለከትነውና ከጓደኛዬ ጋር በአይን ተነጋግረን ተግባባን፡፡ ወደ ሰማይ ቀና ብለን አሸንዳ ለሴቶቿ
የሰጠችውን ፍጹም ነጻነት እኛም ከእግዜር ጠይቀን ወደ ምግብ ቤቱ በመግባት ሁለት ጥብስ አዘዝን፡፡
ጥብሱ ቀርቦ ስንበላ፣ ስንበላ፣ ስንበላ….ቀይተን አላልቅ ስላለ ተውነው፡፡
የመቀሌ ሁለት ጥብስ አዘን ለሁለት ጠግበን በልተን የአዲስ አበባ ሁለት ጥብስ አስተረፍን፡፡
…..
ጎበዝ መቀሌ በምንም አጋጣሚ ከሄድክ በሰው ቁጥር ማዘዝ ያለብህ አልጋ ብቻ
ነው (እርሱንም እንደኔ ከስድስት ጎረምሳ ጋር ከሄድክ ብቻ ነው)፡፡ በተለይ N-1 የሚለው የመንግስት ሰራተኛ ተመጋቢዎች የምግብ
ትዛዝ ቀመር በትክክል የሚሰራው መቀሌ ነው፡፡
…..
አዲስ አበባ የበላነውን ጥብስ ባሰታወስን ጊዜ አለቀስን፡፡ አይ አዲስ አበባ ምን ያለሽው ከተማ ነሽ በይ ብለን ስንረግማት ቆየን፡፡ ሂሳብ ብለን ሂሳቡን
ስናየው ደግሞ በልአምን ከሞቱ ቀስቅሰንና የሱዳን ጠንቋዮችን በዲፕሎማሲ አስመጥተን አዲስ አበባን ማስረገም አማረን፡፡
…..
ከሁሉ በላይ አዲስ አበባ ላይ ቂም እንድንቋጥር ያደረገን ደግሞ የአስተናጋጆቹ
ትህትና ነው፡፡ መቀሌ ውስጥ በገባህበት ሁሉ ወንዱም ሴቷም በፍቅር እና በትህትና ያስተናግዱሀል፡፡ እየተመላለሱ ከጥርስ ላይ ሳይሆን ከልብ ከሚፈልቅ ውብ ፈገግታ ጋር እንደ ህጻን
ልጅ በሚጣፍጥ ኮልታፋ አማርኛ ብላ፣ ምን ይጨመር ይሉሀል፡፡ ጨርሰህ ስትወጣ አመስግነው እና እጅ ነስተው ይሸኙሀል፡፡ ቤትህ እንዳለህ
እንዲሰማህ የማድረግ ጥበባቸው ልዩ ነው፡፡
…..
አዲስ አበባ ሴቷን አስተናጋጅ ፍቅረኛህና ሚስትህ ላይ ደክሞህ የተውከውን
ቁልምጫ እናቱ፣ እሙዬ፣ ቆንጆ ብለህ አቆላምጠህ፤ ወንዱን አስተናጋጅ ጸጉረ ልውጥ ሰው በሰዶም ግብር እስኪጠረጥርህ አባቱ፣ ነብሴ፣
በያ ብለህ እንኳን ቲፕ ይሰጣል አይሰጥም፣ ሱፍ ለብሷል አለበሰም ብለው እንደ ቀንድ አውጣ እየተጎተቱ ይመጡና ተኮሳትረው ይገላምጡሀል፣
ያኔ ደንግጠህ ምን ልታዘዝ ማለቴ ምን ምን አለኝ ትላለህ፡፡
.….
የነዋሪውን ትህትና ስታይ መቀሌ በሙሉ ገዳም ትመስልሀለች፡፡ መንገድ ላይ
ቦታ የምትጠይቀው ሰው መንገዱን ትቶ ሊያሳይህ አብሮህ ይሄዳል፡፡ ጫማ የሚያስጠርገው ብድግ ብሎ፣ ሱቅ ውስጥ ያለው ከሱቁ ወጥቶ፣
ስራ ላይ ያለው ስራውን ትቶ የሚያውቀውን ሊሳይህ የጠየከውን ሊነግርህ ፍቃደኛ ይሆናል፡፡
.….
ሀሙስ ዕለት የመቀሌ ልጃገረዶቸ ፀሀይን ቀድመው ከእንቅልፋቸው ነቅተዋል፡፡
እኛም በልጃገረዶቹ ዜማና ከበሮ ታጅበን ከእንቅልፋችን ነቃን፡፡ ከተማዋ ማታ ካየናት የበለጠ በሴቶቿ ውበት ደምቃለች፡፡ ሆቴልና
ቁርስ ቤቶች ሳይቀሩ በልጃገረዶቹ ወገብ ቀንተው አረንጓዴ የአሸንዳ ቅጠል አሸርጠዋል፡፡
.….
ሰላም ቁርስ ቤት ቁርስ ስንበላ የታዘዘን አስተናጋጅ በቋንቋ ሳንግባባ ቀርተን፣
አንድ ወተትና አንድ ሻይ ብለነው ሳለ ሁለት ወተተወና አንድ ሻይ አመጣ፡፡ ስቀን ዝም ስንል ነገሩ የገባው ሌላ አስተናጋጅ ቀረብ
ብሎ ይቅርታ ጠይቆን ወተቱን ወስዶ ቁጭ ብሎ ጠጣው፡፡ ኋላ ሂሳብ እንክፈል ስንል እንቢ ብሎ የአንድ ወተትና የአንድ ሻይ ብቻ እንድንከፍል
አደረገ፡፡ አዲስ አበባ ቢሆንስ ብቻህን ቁጭ ብለህ አስተናጋጁ 2 ኪሎ ጥብስ አዞኛል ብሎ ካመጣ አመጣ ነው፡፡ ብለህኝ ነው ብሎ
ድርቅ ይልና ያስከፍልሀል፣ይዘልፍሀል፣ ያዘልፍሀል፡፡
.….
በመላው መቀሌ በሄድክበት ሁሉ የሴቶች ጭፈራ ይከተልሀል፡፡ በመንገድ፣ በመዝናኛ
ስፍራ፣ በመንግስት መስራ ቤቶች ሁሉ ያጌጡ ሴቶች በዘፈንና በሳቅ ታጅበው ያስቆሙሀል፡፡ በዚህ የአሸንዳ ወቅት ልጃገረዶቹ ገብተው
ለመጨፈር የሚከለከሉት ቅድስተ ቅዱሳን ብቻ ነው፡፡ በጥንቱ ጊዜ አፄ ዮሀንስ 4ኛ ቤተ-መንግስት ድረስ ሰተት ብለው
ገብተው ይጨፍሩ ነበር፡፡
.….
ልጃገረዶቹ “የኔማ ጋሼ መፋቂያው ወርቅ፣ ሰዓቱ ወርቅ” ብለው በሙገሳ ጭፈራቸውን
ይጀምራሉ፡፡ እነዚህ ልጃገረዶች ብቻህንም ሆነህ መንገድ ላይ ስትሄድ ቢያገኙህ ከበውህ ይጨፍሩና የበዓሉ ተሳታፊ ያደርጉሀል፡፡ አዲስ
አበባ ሴቶች አበባ አየሽ ሆይ ለማለት እና ወንዶች ሆያ ሆዬ ለመጨፈር መብራት ያቆመው መኪና፣ የንግድ ቤቶች፣ የሀብታሞች መኖሪያ
መምረጥ ከጀመሩ ሰነባበቱ፡፡ አዲስ አበባ ከሌለህ ምንም አይኖርህም፡፡ ከሌለህ በራፍህ ላይ ቆሞ አበባ አየሽና ሆያ ሆዬ እንኳን
የሚል ሰው ታጣለህ፡፡
.….
ለልጃገረዶቹ ያለህን ስትሸልማቸው እርጥብ ምርቃታቸውን ያወርዱብሀል፡፡ “ፈሰሰ
ከ’ማይ ነሀሰ” እያሉ ስሜትህን ከፍ ያደርጉታል፡፡ 1 ብርም ስጥ 100 ብር እንደ ነሀሴ ዝናብ ሽልማቱን አፈሰሰው እያሉ ያሞግሱሀል፡፡
.….
ልጃገረዶቹ በሶስቱ ቀናት የሰበሰቡትን የሽልማት ብር ለሁለት ነገሮች ይጠቀሙበታል፡፡
በቅድሚ በቡድን ሆነው ማስታወሻ ፍቶ ይነሳሉ ለጥቀው በቡድን ሆነው ይገባበዛሉ፡፡ በየፎቶ ቤቶች በር ላይ የተሰለፉትን ሴቶች ብዛት
የተመለከተ እንግዳ ሰው የሴቶች ፎቶ መነሻ የመጨረሻው ቀን ሊመስለው ይችላል፡፡
.….
ልጃገረዶች የአሸንዳ ባህል እውነተኛ ንግስቶች ናቸው፡፡ በአሸንዳ ልጃገረዶች
በሁሉም ቦታ ይጨፍራሉ፣ በሁሉም ቦታ ቀንና ሌሊት ይዝናናሉ፡፡ ይህ ሲሆን አንድም ወንድ በውበት ሀይል ተሳስቶና በመጠጥ ተገፋፍቶ
ልጃገረዶቹን ሲለክፍ ባለማየቴ እጄን በአፌ ላይ ጭኛለሁ፡፡ በዚህ እለት ቤተሰብ ለሴት ልጁ ሙሉ ነጻነት ያጎናጽፋል፡፡ ብታመሽ ብሳም
ብታድር በትር የሚያነሳና ፊት የሚያጠቁርባት የለም፡፡
.….
እዚህ ላይ የአዲስ አበባ ወንድ አሸንዳ በዓል ላይ ተገኝቶ ከትግራይ ወንዶች
ልምድ እንዲወስድ እመክራለሁ፡፡ የሸገር ወንዶች እባካችሁ አታስፎግሩን ቢያንስ ሴቶቻችን ብቻቸውን መዝናናት ፈልገው በግልም ሆነ
በቡድን እንደ ሲኒማ፣ ቤተ ተውኔት፣ ካፌና ሬስቶራንት፣ ሆቴል ያሉ የተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች ሲገኙ “ወንድ ፈልገው ነው” ብሎ በመደምደም
እንደ ግሪሳ መክበብና ማዋከብ ይለፈን፡፡ ሄዋንን በየ መንገዱ መዝለፍና መጎተትም ሙድ የለውም፡፡ መቀሌ ሄደን አፈርን እኮ ጎበዝ፡፡
.….
ሀሙስ የበዓሉ ማብቂያ ሶስተኛው ቀን ነው፡፡ ሀውዜን አደባባይ የተዘጋጀውን
የሙዚቃ ኮንሰርት ጨምሮ ልዩልዩ የማሳረጊያ ዝግጅቶች በሆቴሎችና በጭፈራ ቤቶች ተሰናድተዋል፡፡ በኪሳችን የያዝነውን ብር ስለጨረስን
ተጨማሪ ለማውጣት አፄ ዮሀንስ ሆቴል በስተጀርባ ወደሚገኘው የንግድ ባንክ የኤ ቲ ኤም ማሽን ጎራ አልን፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤ
ቲ ኤም ማሽኖች በአብዛኛው በእድልና በጸሎት የሚሰሩ በመሆናቸው የኔና የጓደኛዬ እድል ጠሞ ማሽኑ አልሰራም የሚለውን መርዶ ደረቱ
ላይ በጉልህ ጽፎ አገኘነው፡፡
.….
አዲስ አበባን መርገም በጀመረ አፋችን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ የከፈትንበትን
ቀን ቆመን እየረገምን ሳለን አንዲት የደስደስና ቅርጽ ያደላት ሴት መልአክ “አይሰራም?” አለችን በትግርኛ አማርኛ:: አዎ አላት
ፈጣኑ ጓደኛዬ ፈጥኖ፡፡ ሲገረፍ እናቱ እንደመጣችለት ህጻን ተራ በተራ ንግድ ባንክን አማረንላት ስናበቃ “ኑ እኔ ሌላ ቦታ ላሳያችሁ”
ብላ ይዛን ሄደች፡፡
.….
የአዲስ አበባ ሴቶች ሰዓት ሲጠየቁ እንኳን ይቆጣሉ፡፡ ሁሉ ነገር ለከፋና
ጠበሳ ይመስላቸዋል፡፡ ሀሳብ ለመለዋወጥና ከጾታ የጸዳ ጓደኝነት ለመመስረት አስቸጋሪዎችም አሰልቺዎችም ናቸው፡፡ ልጅቷን ስለ አሸንዳ በዓል ስለ መቀሌ ከተማ አንዳንድ ነገር እየጠየቅናት በፈገግታና
በደግነት እያስረዳችን የኤ ቲ ኤም ማሽን ያለበት ቦታ ደርሰን ብር
አወጣን፡፡
.….
ልጅቷ በሚገርም የዋህነት “መንገዱ እንዳይጠፋችሁ ወደ ከተማ እመልሳችኋለሁ
በፊት ግን ኑ ማርያምን እንሳለም” አለችን:: ማርያምን ስንሳለም እንዲህ ብዬ አመሰገንኩ “አቤቱ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን፡፡
ተራሮች ሳይወለዱ፣ምድርም አለምም ሳይሰሩ፣ ከዘላለም እስከዘላለም ድረስ አንተ ነህ፡፡”
.….
ከሀውዜን አደባባይ የበዓሉ ርችት ተተኮሰ፡፡ ሶስታችንም ማሪያም ቤ/ያን
ፊት ለፊት ቆመን ብርሀኑ ወደ ሰማይ ተመንጥቆ ሲበተን ተመለከትነው፡፡ በብርሀኑ ህብርና ፍንጣቂ ቋንቋ፣ ዘርና ባህልን ገድፈን በአንድነት
ተደሰትን፡፡
.….
ደጓ ልጅ የነበርንበት ቦታ መልሳን ወደ አሸንዳዋ ሄደች፡፡
.….
ቀን ልጃገረዶቹ የመረቁት ምርቃት ምሽት ላይ ደርሶ የነሀሴ ሰማይ ዶፉን
አፈሰሰው፡፡ የከተማዋ የኮብል ስቶንና የአስፋልት መንገዶች ወደ ትናንሽ ጅረትነት ተቀየሩ፡፡
.….
እኔና ጓደኛዬ ግን መቀሌን የበለጠ ተዋብንባት፡፡ ጅረቱ የዮርዳኖስ ትልቅ
ወንዝ ሆኖ በደግነት፣ በንጹህነትና በየዋህነት ውሃ ላይ አንሳፈፈን፡፡ ወንዙ ወስዶን፣ ወስዶን፣ ወስዶን ሲያበቃ የሳቅ መዐበል ውስጥ
ቀላቀለን፡፡ በመዐበሉ ሳቅ ስቀን፣ ስቀን፣ ስቀን ስናበቃ በአባ ኪሮስ ምልጃ በውብ ኩርፊያና ኩራት ደመቅን፡፡ ዘፋኙ እኛን አይቶ
“ከከንፈርሽ
ላይ ጽጌሬዳ ሳይ፣ ከራሴ ጋራ እስከምለያይ
በፍቅር ፈዝዤ ጠፍቶኝ ማረገው፣
አይኔን ካፍሽ ላይ ጣል ባደርገው
ሳማት ሳማት አለኝና ቀልቤን ገዛው እንደገና፣
ሳሙኝ ሳሙኝ የሚል ከንፈር፣ ድንገት አጉል አድርጎኝ ነበር፡፡”
.
.
.
ልብ አሸፍቶ፣ ቀልብ ያሰውራል፣
ቁንጅናሽ ለጉድ ያምራል፡፡
ያምራል….ያምራል…ያምራል…. ሲል
……
የዬርዳኖስን መዐበል በደጓ ሴት ውበት ንቀን፣
የአባ ኪሮስን ምንኩስና በምህረት ደግነት ገሰን፣
በመጨረሻው የአሸንዳ ሌሊት ጭፈራ ታጅበን፣
ለነገው የሸገር ጉዞ እንደነቃን ተጋደምን፡፡
……
አንቺ ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ ተመለሽ
እናይሽ ዘንድ ተመለሽ ተመለሽ፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ