ከ “ተደምሬያለው!!” ባሻገር
ከ “ተደምሬያለው!!”
ባሻገር
የሴት
አያቷና የገጠር ነገር የማይሆንላት ጋደኛዬ መንፈሷ ዝቅ ሲልባትና መነቃቃት ሲያሻት ሁልጊዜም ወደ አያቷና ወደ ገጠር ትኖጣለች፡፡
ጋደኛዬ ልክ እንደ በአሉ ግርማ ሁሉ “ከተማ በድንጋይ ክብር የተሞላ ህይወት አልባ መካን ነው” የሚል ከተማ ጠል የሆነ ደረቅ ፍልስፍና
አላት፡፡ ሁሌም ሲመቸኝ እንደማደርገው በዚህኛውም የአዲስ ዓመት መባቻ ከእማሆይ ትርሲት የእውቀት ሁዳድ የአመት ድርጎዬን ለመቀበል
ጋደኛዬን ተከትዬ ፍቼ መዳረሻ ላይ ከምትገኘው ከውቧ ቅዬ ከደብረ-ጽጌ ተገኝቻለሁ፡፡
በአንዱ
አመሻሽ እኔና እማሆይ ትርሲት ከደጅ ተቀምጠን ስለ ሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታና ስለ መሪያችን ዶ/ር ዐብይ እያወጋን ባለንበት፤ ጋደኛዬ
አለም ድንቡሽቡሹን ልጇን ክረምቱን ለአንደኛ ክፍል ለማዘጋጀት በማሰብ ሒሳብ ስታስጠናው አልፎ አልፎ ድምጿ ከቤት ውስጥ ይሰማናል፡፡
ከግማሽ ሰዓት ያህል በኋላ ጓደኛዬ ውብና ትላልቅ አይኖቻ እንደ ክረምት ወንዝ ደፍርሰው ደፍርሶና ቢጫ ፊቷ በርበሬ መስሎ “የማሪያም
ጣቷን” ጥፍር በጥርሷ እየበላች አጠገባችን ተቆናጥራ ቁጭ አለች፡፡
አያቷ
ሁኔታዋን ከፊቷ ላይ በመረዳት ከኔ ጋር የጀመሩትን ወሬ እንኳን ሳይጨርሱ “አይዞሽ ትምህርት በችኮላና በእልህ አይሆንም፡፡ ደግሞም
ልጅ በራሱ መንገድና ፍጥነት ነገሮችን ፈቅዶ መረዳትና መማር ሲችል ነው ጥሩ፡፡ ትምህርት ከየዕለት ኑሮና የህይወት ጉዞ ጋር ካላገናኙት
የሚሸመደድ እንጂ የሚረዱት ሊሆን አይችልም፡፡ ልጅን ሲያስተምሩም ሆነ ሲያስጠኑ እኔን እንዳስተማሩኝ ቆርቆሮ የሁለተኛ ደረጃና የዩንቨርሲቲ
መምህራን አይነት በቀቀን ሆኖ መቅረብ ትውልድና ሀገርን ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ተማሪዎች ወይም ልጆች የሚማሩት ትምህርት ሙት እንዳይሆንባቸው
በመጀመሪያ የትምህርቱን ጽንሰ ሀሳብ ከሚያውቁትና ከሚኖሩት አለም ጋር አዋህደ እንደ ዋዛ መተረክ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ልጅሽን የምታስጠኚው
መሰረታዊ የሒሳብ ትምህርት ደግሞ ለዚህ የተመቸ ነው፡፡ ምክንያቱም የሒሳብ ጽንሰ ሀሳብ ከፍጥረታት አፈጣጠርና አኗኗር ጋር የተገመደ
በመሆኑ ነው፡፡” ብለው ልጃቸውን ገሰጹና አኔን ደግሞ በሹፈት ፊት እየገረመሙ “አይደለም እንዴ መምህሩ?” ብለው የለበጣቸውን ፈገጉልኝና
ፈጠን ብለው “ነገርን ነገር ያነሳዋል” እንዲሉ እሰቲ አንዲት ጥያቄ ልጠይቃችሁ? ለመሆኑ ተደምራችኋል? አሉ እማሆይ ከንፈራቸው
ላይ የተንጠለጠለውን ሳቅ በነጠላቸው በግድ አፍነው እየመለሱት”
“እንዴ
አዎ ተደምረናል” አልኩ ቆፍጠን ብዬ::
“ቀላል
መደመር ድምር ነው ያልኩት” ስትል መለሰች ጓደኛዬ ንዴታን እረስታ፡፡
እማሆይ
ፈገግታቸው ከከንፈራቸው ላይ እንደተሞሸረ “ዶ/ር ዐብይ አስቦበት ነው ስለመደመር የሚያወራው፡፡ እስካሁን የወሰናቸው ውሳኔዎቹና
ለነገሮች ሚሰጠው ምላሽ የመደመር (+) የሒሳብ ስሌት ካለው ጠባይ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ታዲያ እናንተስ ተደምረናል ያላችሁት
በቅዲሚያ የመደመር (+) የሒሳብ ስሌት ጠባይ ባለቤት እንደሆናችሁና የምትደምሩት ነገር እንዳላችሁ አረጋግጣጭሁ ነው ወይስ እንደ
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በስሜታችሁ ተነድታችሁ? ለመኖኑ ጠባያችሁ ሒሳባዊ የጠባይና የማንነት ምልክት ሲይዝ የናንተን ጠባይ ከመደመር፣
ከመቀነስ፣ ከማባዛትና ከማካፈል የትኛው ይገልፀዋል?” ሲሉ ጥያቄ በጥያቄላይ ደራርበው አፈጠጡብን፡፡
ሁለታችንም
እኩል “አል..ገባኝም፡፡” አልን ግራ በገባው ድምጽ፡፡
”አይ ልጆቼ “ቃላት ይገላል ትርጉም ግን ያድናል” ሲባል አልሰማችሁም? ታዲያ በሒሳብ ስሌት ውስጥና ከሒሳብም
ስሌትም በላይ ያለውን የመደመርን ትርጉም በቅጡ ሳናውቅ በተለይ ደግሞ እያንዳንዳችን የራሳችንን ጠባይና ሚና በሒሳብ መነጽር ውስጥ
ተንትነን ሳንረዳ በሾላ በድፍን “ተደምሬያለው” ብሎ ማለት ለዐብይም ሆነ ለኢትዮጵያ ምን ሊፈይድላቸው ነው” ብለው ያፈኑት ሳቅ
አምልጧቸው በድዳቸው ተንከትክተው ስቀው የቀሰቀሱትን ትንታ ሲያስታግሱ ቆዩና ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡
“እንደኔ
እንደኔ ከሁሉ በፊት በራሳችን ተነሳሽነት እያንዳንዳችን የገዛ ጠባያችንንና ለመደመር ጉዞ ልናበረክት የምንችለውን የየግል አስተዋጾ
በመሰረታዊ የሒሳብ ስሌቶች ምሳሌነት አውቀን መለየት አለብን ባይ ነኝ፡፡ ሁላችንም በጠባያችን አማካኝነት አንድ ወይም ሁለት መሰረታዊ
የሒሳብ ስሌቶችን ወክለን ነው እለት እለት የምንቀሳቀሰው፤ እኔ መሰረታዊ የሒሳብ ስሌቶችን በመጠቀም የሰውን ልጅ ጠባይ ስተርክላችሁ
እናንተ ደግሞ የየራሳችሁን ምልክት ፈልጋችሁ በማግኝት በመደመር ጉዞ ውስጥ ማን እንደሆናችሁና ሚናችሁ ምን እንደሆነ በግልጽ ለማወቅ
ሞክሩ፡፡” አሉ እማሆይ፡፡ እኔና ጓደኛዬ ጋሽ ስብአት ገ/እግዚሐብሄር እንደሚለው “ሰውነታችን ሁሉ ጆሮ ሲሆን” እማሆይ ቀጠሉ፡፡
መደመር (+) ፡- መደመርን ምልክታቸው ያደረጉ ሰዎች ዋነኛ መለያ ጠባያቸው የራሳቸውን
የሆነና ሌላው ላይ መጨመር የሚችል ጠቃሚ ድርሻ ያላቸው መሆናቸው ነው፡፡ የመደመር ሰዎች የሀገር፣የተቋም ወይም የግለሰብ እውቀት
ላይ ተጨማሪ እውቀት፣ ተጨማሪ ገንዘብ፣ ተጨማሪ ሰላም፣ ተጨማሪ ፍቅር የሚጨምሩ ወይም መጨመር የሚችሉ ናቸው፡፡
የመደመር
ጠባይ ያላቸው ሰዎች የመደመር ወይም የጨማሪነት ጠባያቸው በመካሪነት፣ በአሰልጣኝና በኮትኳች ችሎታና ክህሎቶቻቸው እየታገዘ የትዳር
ወይም የንግድ አጋራቸውን ብሎም ተቋምና ሀገርን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚችሉ ብርቱ መሪዎችና ተጓዳኞች ናቸው፡፡ ታዲያ ጠቅላይ
ሚኒስቴራችን እንደመር ሲል ይህ አይነቱ ጠባይ ያላችሁ ሁኑና ከትናት የተሸለ ሀገራዊ ሰላም፣ፍቅርና አንድነት እንዲሁም የላቀ ኢኮኖሚያዊ
እድገት እናስመዝግብ እያለ ይመስለኛል፡፡ ልጆች መደመር ተደምሬያለው ብሎ ቲ-ሸርት ከመልበስና ከመፈከር በዘለለ የራስ ሚናን ማወቅና
እጄ ከምን ማለትን ይጠይቃል፡፡ የተደመረ ሰው የሌላውን ሀሳብ ሳይፈርድ ማዳመጥ ይችላል፣ የተደመረ ሰው በንግግሩ ከ”እኔ” ይልቅ
“እኛ” ይቀናዋል፣ የተደመረ ሰው ከቤተሰቡ፣ከጋደኞቹ፣ከጎረቤቶቹ፣ከህብረተሰቡና ከሀገሩ ህዝቦች ጋር ብሎም ከአለም ህዝቦች ሁሉ ጋር
በመተባበርና በፍቅር ይኖራል፡፡
ድምርን የጠባዩ ምሳሌ ያደረገና የተደመረ ተማሪ ራሱን ከስንፍና በማራቅ ጠንክሮ የመማርን ግብር በመደመር ለሀገር
ተስፋ መሆን አለበት፣የተደመረ ወጣት ከሱስና ከሞራል ኪሳራ ራሱን ነጻ የማውጣትና ሌት ተቀን የመስራትን ወኔ መደመር አለበት፣ ሌባውና
ደላላው ከተደመረ በቅንድቡ ወዝ መኖርን መደመር አለበት፣የተደመረ የመንግስት ሰራተኛ ቢሮክራሲና ሙስናን በመስበር ከልብ አገልጋይነትን
መደመር አለበት፣የተደመረ የመንግስት ባለስልጣን ሆዱን ገቶ ለመልካም አስተዳደር መስፈን መሰጠትን መደመር አለበት፡፡ ያለዛ መደመር
ከንቱ ልፍለፋ ሆኖ ነው ሚቀረው፡፡ ኦሮሞ ከአማራው ጋር ከተደመረ፣ትግሬው ከደቡብ ጋር ከተደመረ፣ሱማሌው ከቤኒሻንጉሉ ጋር ከተደመረ፣
ሐረሬው ከአፋሩ ጋር ከተደመረ ውጤቱ ታላቋ ኢትዮጵያ ናት የምትሆነው፡፡ ሌላ የምንመለከተው ታላቅ ነገር አይኖረንም፡፡
ልጆቼ
የሰው ጠባዩ ረቂቅ ነው ምልክቴ መደመር ነው እያለና ስለመደመር ሌት ተቀን እየፎከረ የራሱ የሚለው የሚደምረው ነገር የሌለው አጉዳይና
ዜሮ (0) ደማሪ አስመሳይ ሰው እንዳለም ማወቅና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ አሁን የመጣውን ለውጥና መንግስት እየፈተኑ ካሉ ግለሰቦችና
አካሎች አንዳንዶቹ እነዚህ ዜሮ ደማሪዎች ይመስሉኛል፡፡
መቀነስ (-) ፡- አለም የሁለትዮሽ ህግን ተከትላ የተሰራች በመሆኗ የጠባይ ምልክታቸው
ከመደመር በተቃራኒ የሆነ ግለሰቦችንም ይዛለች፡፡ መቀነስን ምልክታቸው ያደረጉ ሰዎች ዋነኛ የጠባይ መለያቸው ሁሉን ማሳነስ ነው፡፡
ሁሉ አይጥሜ ሆነው በመቅረብ ያዩትንና የሰሙትን ሁሉ የመንቀፍ፣ የመተቸትና የማጣጣል አባዜ የተጠናወታቸውና የሰውን ተስፋ፣ ምኞትና
ሙከራ ሁሉ በማጣጣል ስራ የተጠመዱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች መሪ ቢሆኑ ታሪክ አርክሰው የህዝብና የሀገር ክብር ያዋርዳሉ፣ሀገር ይገነጥላሉ
ያስገነጥላሉ፣ ሰራተኞችን ያባርራሉ፣ ህብረተሰብን ከቅዬው ያፈናቅላሉ፡፡ የትዳርና የንግድ አጋር ቢያደርጓቸው ደግሞ ትዳር ይበትናሉ፣ንግድ
ያከስራሉ፡፡ የመቀነስ ሰዎች ከአንድነት ይልቅ በመበታተን ያምናሉ፣ያለው ላይ ጨምሮ ከማተለቅ ይልቅ ከአዲስ መጀመርና መባከን ያዞትራሉ፡፡
የማሳነስ
ሰዎች በመደመር ሰዎች መገራትና መለወጥ ካልቻሉ ለመደመር ጉዞ እንቅፋትና ተቃራኒ ሆነው መቀጠላቸው ስለማይቀር ከልብ የመነጨ ፍቅር
ሊሰጣቸውና ይቅርታ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ በተለይ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ጠባያቸውን ማሻሻልና መለወጥ እንዲችሉ የቀለምና ተግባር
ትምህርት ያስፈልጋቸዋል፡፡
ማካፈል (-፡-) ፡- ሶስተኛው የሰውን ባህሪ ሊገልጽ የሚችለው መሰረታዊ የሂሳብ
ስሌት ማካፈል ነው፡፡ በዚህ የሒሳብ ስሌት ጠባያቸው ተመስሎ ምልክታቸው ያደረጉት ሰዎች በልግስናቸው ብዛት ይታወቃሉ፡፡ ስግብግብነትና
ሆዳምነትን በፍቅር ያሸነፉ ጻድቃኖች ናቸው፡፡ የማካፈል ጠባይ ያላቸው ሰዎች ሲሰጡ እንደሚበዛላቸው በጽኑ ስለሚያምኑ ገንዘባቸውን፣
ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ፍቅራቸውን፣ ጊዜያቸውን ለአገርና ለወገን ለማካፈል አይሰስቱም፡፡
ሀገራችን ዳግም ካንቀላፋችበት ለመንቃት በተንጠራራችበት በዚህ ወቅት ማካፈልን ምልክታቸው ያደረጉ ለጋስ ዜጎች
ያስፈልጓታል፡፡ ለምሳሌ ብቻውን መበልጸግ የማይፈልግ ባለሀብት፣እውቀቱን ከልቡ ለማካፈል ጥቅማ ጥቅምን የማያስቀድም ምሁርና ባለሙያ፣ስልጣን
የማይሰስት መንግስትና የመንግስት ባለስልጣን ለመደመር ጉዞ መሳካት እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች ለብዙ ማካፈል መቀነስ ይመስላቸውና ይሰስታሉ ነገር ግን
አካፍሎ የጎደለበት ሰጥቶ ያልተጨመረለት ሰው ፈጽሞ የለም፡፡
በማካፈል
እና በመከፋፈል መካከል ያለውን የጠባይ ልዩነት ግን ልብ ማለት ይገባችኋል፡፡ ማካፈልን ምልክታቸው ያደረጉ ጠባያቸው ግን ከፋፋይነት
የሆነ አሳናሾች መኖራቸውን አውቆ መጠንቀቅ ግድ ነው፡፡
ማባዛት (X)፡- ልጆቼ መልካም ነገርን ለይቶ የማብዛት ጸጋን መታደል ምንኛ መመረጥ
መሰላችሁ፡፡ ጠባያቸው በማባዛት ምሳሌነት የሚገለጥ ሰዎች ብሩህ አእምሮና አስተዋይ ልቦና ስላላቸው ጥቂቱ ነገር እልፍ ይሆንላቸዋል፡፡
እነዚህ ሰዎች እግዚሀብሄር የሰጣቸውን መክሊትና የቀለምና የተግባር ትምህርታቸውን ተጠቅመው ነግደው ያተርፋሉ፣ ተምረው እልፍ ያስተምራሉ፡፡
ሰልጥነው ሺህ ያሰለጥናሉ፡፡ ምንምን አንድ ነገር አንድ ነገሩን ደግሞ ሁሉም ነገር ያደርጉታል፡፡ ኢትዮጵያ ትንሽ ሀሳብን ግዙፍ ቁስ ወይም ረቂቅ አገልግሎት አርገው የሚያበዙ የፈጠራ ሰዎችና ኢንተርፕረነሮች፣
ጥቂት ትምህርታቸውን ምርምርና መፍትሄ የሚያደርጉ ምሁራን፣ ውስኑን ሀብት በፈጠራ በመጠቀም ውጤታማነትን የሚረጋግጡ የሀገርና የተቋም
መሪዎች፣በስብከትና በትምህርታቸው ትንሹን ፍቅርና አንድነት ዝሆን የሚያሳክሉ የሀይማኖት ሰዎች ከሁሉ በላይ በዳዴ የጀመርነውን የመደመር
ጉዞ ወደ እርምጃ የሚያሳድጉ እርምጃውን ደግሞ እሩጫ የሚያደርጉ አብዢ ጠባይ ያላቸው ሰዎች በሁሉም መስክ ያስፈልገናል፡፡
የመደመር ጎዞ በቶሎ ወደማብዛት ጉዞ ካልተቀየረ ፈጣን እድገት ማረጋገጥ አይቻልም፡፡
ልጆች
ልክ የዜሮ ደማሪ ጠባይ እንዳላቸው የመደመር ሰዎች ሁሉ የማብዛት ምልክት ይዘው የማብዛት ጠባይ ግን የሌላቸው ምንም እንዳትሏቸው
ቁጥር ነኝ ባዬች ቁጥር እንዳትሏቸው ደግሞ ዜሮዎች ሆነው ነገሮችን ሁሉ በዜሮ ለማባዛት የሚጥሩ ስለሚኖነሩ ከነዚህ ሰዎች ጋር ከመደመርም
ሆነ ከመብዛት በፊት ከንግግርና ፉከራቸውን አስቀድሞ አበርክቶና ሀሳባቸውን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም መጥፎውን ነገር ብቻ
የማብዛት ጠባይ ያላቸው ጠብን ጦርነት፣ መሳምን ንክሻ የሚያሳክሉ ቂመኞችና የቁርሾ ሀውልትና የቂም ግድግዳ ግንበኞች የሆኑ አሉታዊ
አብዢዎችም እንዳሉ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
ልጆቼ
ልብ በሉ አንድ ሰው ሙሉ ሰው ለመሆን ካንድ በላይ በጎ ጠባይ ያለው መሆን ይገባዋል፡፡ ደምሮና ተደምሮ የሚጨምር፤ አሰቦና ፈጥሮ
የሚያበዛ እንዲሁም አካፍሎ የሚያሳድግ አሉታዊ ጠባይ ያለው ሰው ሙሉ ሰው (የመደመር ጉዞ ትክክለኛው ሰው) ይባላል፡፡
ጠባይ
እንደ ባህሪይ ተፈጥራዊ ስላይደለ በልምምድና በጊዜ ለመሻሻል ይችላል፡፡ ጠባይ በቀለም ትምህርትና በተግባር ልምምድ ይለወጣል፡፡
የራስ ፍቃድና ተነሳሽነት ካለ በተለይ በተለይ ለሀገርና ለወገን አንዳች መልካም ነገር የማድረግ ፍላጎት ካለ ቀናሾች ወደ ደማሪነት፣ከፋፋዮች
ወደ አካፋይነት፣ አሳናሾች ደግሞ ወደ አብዢነት በመለወጥ የመሰረታዊ ሒሳብ ምልክታችንን መለወጥና ጠባያችንን ማሻሻል እንችላለን፡፡”
ብለው
እማሆይ ትርሲት እኔና ጋደኛዬን ከተቀመጥንበት ጥለውን ገቡ፡፡ እኛም በመደመር ጉዞ ውስጥ ስላላን ምልክትና አበርክቶ ስናስብ በደብረ-ጽጌ
ጥቁር የክረምት ሰማይ ላይ ውብ ጨረቃ ከአዲሱ አመት አዲስ ተስፋ ጋር ስትፍለቀለቅ አየናት፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ