ጥምቀት፣ እግዜርና ውኃ
ጥምቀት፣
እግዜርና ውኃ
እንኳን ለብርሀነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፡፡ ጥምቀት የውኃ በአል ነው፡፡
በሌላ በኩል ጥምቀት ወይም ኤጲፋንያ መገለጥ መታየት ማለት በመሆኑ ጥምቀት የመገለጥ ወይም አስተርእዮ
በአል ነው፡፡
እንደ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ከህዳር 11 እስከ ህዳር17 ወይም
እስከ ጾም ነነዌ ያለው ጊዜ የአስተርእዮ (የመገለጥ) ጊዜ ይባላል፡፡ ሊቃውንቱ እንደሚናገሩት ዘመነ አስተርእዮ
በሚባለው
በዚህ ወቅት አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ፣ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና
የሦስትነት ምሥጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው
ሠርግ ላይ የመጀመሪያው ተዐምር በመፈጸሙ፣ አምላካዊ ኃይሉ መገለጡ እየታሰበ
ምስጋና ይቀርባል።
ከነዚህ ሶስት ዋና ዋና የመገለጥ ክስተቶች ሁለቱ ከውኃ ጋር የተገኛኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ ስለውኃ
የታወቁ ሳይንሳዊ እውነቶችን ከሀይማኖታዊ አስተምሮቶች ጋር በማቀኛጀት ለማውራት ከዚህ ወቅት የተሸለ ሌላ አጋጣሚ አላገኝም፡፡
***
በምድራችን ላይ ለቁጥር የሚታክቱ የተለያዩ የእምነት አስተምሮቶች
ላይ የተመሰረቱ በርካታ ሀይማኖቶች አሉ፡፡ በሚገርም ሁኔታ እነዚህን ሀይማኖቶች የሚያግባባ አንድ ነገር ቢኖር ውኃ ብቻ ነው፡፡
እንደ ክርስትና እስልምና ሂንዱዚም ቡዲዝም ሺቶይዝ እና ሌሎቸም ታላላቅ ሀይማኖቶች ውኃን የሀይማኖታዊ ስርአቶቻቸው ማእከል አድርገው
ይጠቀሙበታል፡፡
ይህ የጥምቀት በዓል በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንት ተከታዮች
ዘንድ የሚከበር በመሆኑ ኦርቶዶክሳዊ አስተምሮቶችን መሰረት አድርጌ ሳይንሳዊ ግንቶችን እያጣቀስኩ ስለ ውኃ አወጋለሁ፡፡
***
መጽሀፍ ቅዱስ እንደሚነግረን እግዚሀብሄርን ያየው አንድስ እንኳን
የለም፡፡ ልብ ላለው ይላሉ የሀይማኖት አባቶች የእግዚሀብሄር አምላክ ማንነትና ባህሪና በፍጥረቱ ይታወቃል፡፡ እናም የሚታየው ተፈጥሮ
የማይታየውን መንፈሳዊ አለም ያብራራል ለዚህ ደግሞ ከውኃ የተሻለ ድንቅ ፍጥረት አላገኝውም፡፡ ውኃን ልብ ብሎ ለመረመረ የአምላክን
ባህሪ ለማወቅ ይቻለዋል፡፡ ለዚህ ይሆን በመጽሀፍ
ቅዱስ ከ ዘፍጥረት እስከ ዮሀንስ ራዕይ ከእምነት፣ ፀሎት እንዲሁም ሀይማኖት ከሚሉት ቃላቶች በላይ 722 ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኝ ብቸኛው
ቃል ውኃ ብቻ የሆነው፡፡
***
ለኔ ስለ እግዚሀብሀር ህይወት ሰጪነት፣ማህሪነትና ቁጣ እንዲሁም
አካላዊና መንፈሳዊ ማንነት እንድናውቅ ከብርሀን፣ ከአንበሳና ንስር በላይ በምድር ላይ የተሰጠን ምሳሌ ውኃ ነው፡፡ ስለምን ይህንን
እንዳልኩ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ከሀይማኖታዊ አስተምሮቶች ጋር እያነጻፀርኩ ላስረዳ፡-
1.
ውኃ
የህይወት መገኛ ነው፡-
ሳይንስ
በሌላ አለም ህይወት መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ መጀመሪያ የሚፈልገው ውኃ መኖር አለመኖሩን ነው፡፡ ውኃ ካለ ህይወት አለ፡፡ ሳይንስ
ጽንስ ከተጸነሰ በኋላ ለማደግና ለመጎልበት የሽርት ውኃ ታላቅ አስተዋጾ እንዳለው ይናገራል፡፡ ፈላስፋው ታለስ የመጀመሪያው ፍጥረት
የተገኘው ከውኃ እንደሆነ ሲናገር ታላቁ ሰአሊና ሊቅ ሊዮናርዶ ዳቪነቺ ውሀን (the driving force of all
nature) ወይም የተፈጥሮ ሁሉ መዘወሪያ ሀይል ይለዋል፡፡
መጽሀፍ
ቅዱስን ገና ስትገልጠው (በዘፍጥ 1፡2) ይህንንኑ ስለውኃ ሳይንስ ያረጋገጠውን እውነት እያወራ መጀመሩ አጋጣሚ አይደለም “በመጀመሪያ
የእግዚሀብሄር መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር ይላል፡፡” ከጸሀይ፣ ከጨረቃና ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ በፊት ውኃ የተጠቀሰው የህይወት
መገኛ በመሆኑ ነው፡፡ ከዛም ወረድ ብለህ ስታነብ (ዘፍ 1፡20) ውኃ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሰውን ሁሉ ታስገኝ ይላል፡፡
ውኃ የህይወት ምንጭ በመሆኑ መጽሀፍ ቅዱስ ዘላለማዊውን ይህወት
የሚሰጠውን አማላክና የአምላክን ቃል በውኃ መስሎ ያቀርባል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃ አጠጪኝ ብሏት ለነፈገችው ሳምራዊት ሴት “እኔ
የህይወት ምንጭ ነኝ እኔ ከምሰጠው ውሀ የሚጠጣ ለዘላለም አይጠማም“ ብሎ ቃሉንና መንፈሱን በውኃ መስሏልና፡፡
ሳይንስ እንደሚለው ሰው በስጋዊ ህይወቱ ለመኖር በቀን ቢያንስ
2.5 ሊትር ውኃ መጠጣት አለበት መጽሀፍ ቅዱስ በበኩሉ ሰው በመንፈሳዊ ማንነቱ እረክቶ ለመኖር በየለቱ የእግዚሀብርን ቃል መጠጣት
ይኖርበታል ይለናል፡፡
2.
ውኃ
የማንጻትና ነጻ ስሜት የማጎናጸፍ ሀይል አለው
በውኃ በመታጠብ አካላዊ እድፋችንን እናነጻለን፣ልብሳችንና እቃዎቻችንን
እናጥባለን አዲስ እናደርጋቸዋለን፡፡
የቤተክርስትያን አባቶች ጥምቀትን ከመቀብር ጋር ያያይዙታል ሰው
በውኃ ሲጠመቅ ለቀድሞ አኗኗሩ ይሞትና አዲስ መንፈሳዊ ማንነትን ይላበሳል እንዲሉ፡፡ በጥምቀት በአል ውሃውም ተባርኮ ሕዝቡ ሲረጭ የክርስትና ስማቸውንም
የረሱ ወደካህናቱ
ይቀርቡና አዲስ የክርስትና ስም ይቀበላሉ።
በውኃ ስንታጠብ ወይም ውኃ ዳር ስንሆን ውኃ ለአእምሯችን የነጻነት
ስሜት እንደሚሰጠን ሁሉ ጥምቀት ከነጻነት ጋርም ይያያዛል፡፡ በክርስትና
የጥምቀት አመጣጥ ከሙሴ የኤርትራን ባህር ከፍሎ እስራኤላውያንን ከግብጽ ከባርነት ነጻ ማውጣት ጋር ይያያዛል፡፡ ሙሴ እስራኤላውያንን
የኤርትራን ባህር ከፍሎ እንዳሻገራቸው ሁሉ ክርስቶስ በእደ ዮሀንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ የእዳ ደብዳቤያችንን በመቅደድ ከዳቢሎስ
ምርኮኝነትና ከሀጢያት ባርነት ነጻ አወጣን እንዲሉ፡፡ እንግዲህ ወኃ ባፋዊ የሆነውን የሰውን አድፍ ሲያነጻ እግዚሀብሄር ደግሞ የሰውን
መንፈሳዊ እድፍ (ሀጢያትን) ያነጻል ማለት ነው፡፡
3.
ውኃ ወደውስጡ የጠለቀውን ነገር በሙሉ ይሞላል
እኔም አንተም እንደምናውቀው አፉ ክፍት ሆኖ ቀዳዳ የሌለው ማንኛውም
ነገር ወደ ውኃ ውስጥ ቢጠልቅ ውኃው የጠለቀውን ነገር ይሞላዋል፡፡
ይህንን የውኃ ባህሪ ወደ አምላክ ባህሪ ስንመልሰው ጥምቀትን እናገኛለን፡፡
በውኃ መጠመቅ ወንድ ልጅን በዐርባ ቀን ሴት ልጅን በሰማንያ ቀን በውኃ ውስጥ በማጥለቅ በመንፈስ ቅዱስ መሞላትንና በጸጋ የሥላሴ ልጅነትን ማግኘትን ያመሰጥራል፡፡ ወይም ካደግን በኋላም ቢሆን በአምላክ
ያመነ ሰው ልቡን ክፍት አድርጎ ያለጥርጥር ውኃ ውስጥ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ቢጠልቅ የእግዚሀብሄር መንፈስ መላ ሰውነቱን
ይሞላዋል፡፡ ልብ በሉ ውኃ የጠለቀበትን ነገር ሁሉ የመሙላት ባህሪው እግዚሀብሄር ያመነበትን ሰው ሁሉ በቅዱስ መንፈሱ የሚሞላ አምላክ
የመሆኑ ምሳሌ ሆነ ማለት ነው፡፡
***
ሳይንስ እንደሚለን ውኃ የራሱ ቅርጽና ቀለም የለውም፡፡ የተቀበለውን
የማንኛውንም ነገር ቅርጽ ይይዛል እንጂ፡፡
መጽሀፍ ቅዱስ እንደሚነግረን እግዚሀብሄር አካላዊ ቅርጽና ቀለም
የለውም፡፡ በዚህም ምክንያት አይመስላችሁም የነጩ፣ የጥቁሩ፣ የቢጫው ስው ቀለም ቀለሙ ሆኖ፤የወፍራሙ፣የቀጭኑ የአጭሩና የረዥሙ ሰው
ተክለ ቁመና ቁመናው ሆኖ ሰው ሁሉ የእግዛብሄር አምሳል መሆን የቻለው?
4. በሶስት የተለያዩ ቅርጾች (form)
የሚገኝ ብቸኛ ነገር ውኃ ብቻ ነው
ሳይንስ በሶስት የተለያዩ ቅርጾች ማለትም ፈሳሽ፣ጠጣርና
ጋዝ ሆኖ የሚገኝ ብቸኛው ምድራዊ ነገር ውኃ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በረዶው ፈሳሽ ውሃና ጋዝ ነው፣ ፈሳሹ ውኃ ጋዝና በረዶ ውኃ
ነው፣ ጋዙ ፈሳሽና በረዶ ውኃ ነው አንዱ ባንዱ ውስጥ አለ፡፡
ይህንን
የውኃ ባህሪ ወደ ኦርቶዶክሳዊ አስተምሮት ስንቀይረው የምን ምሳሌ እንደሚሆን መገመት አይከብድም፡፡ በዚህ በጥምቀት በአል ለአለም
ከተገለጡ አምላካዊ ሚስጢሮች መካከል አንዱ የአምላክ የሶስትነት ሚስጢር ወይም የስላሴ ሚስጢር ነው፡፡ እግዚሀብሄር ወልድ በዮርዳኖስ
ባህር ሲጠመቅ እግዚሀብሄር አብ በደመና የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት ሲል እግዚሀብሄር መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በእርግብ አምሳል
በራሱ ላይ አርፏል፡፡ እናም ውሃ የስላሴን የሶስትነት ባህሪ በመግለጽ የሚስተካከለው አለ ትላላችሁ?
የሚገርመው
ሳይንስ ለምንና እንዴት ውኃ ብቻ በሶስት የተለያዩ ቅርጾች እንደሚገኝ ማረጋገጫ ወይም ማስረጃ እንዳላገኘ ሁሉ እኔ እስከማውቀው
በምሳሌ ለማስረዳት ከመሞከር በላይ የስላሴን የሶስትነት ሚስጢር መርምሮ የሚያስረዳ የሀይማኖት አባትና ሊቅ አልተገኘም፡፡
5. ከባድ ነገር መሸከምና ማንሳፈፍ የሚችል ጥንካሬ
ያለው ፈሳሽ ውኃ ብቻ ነው
ሳይንስ
ጠንካራ surface tension ያለው ፈሳሽ ነገር ውኃ ብቻ መሆኑን ያረጋግጣል በዚህም ከትናንሽ ነብሳት እስከ ከባባድ ጓዝ የጫኑ
ትላልቅ መርከቦች ሳይቀሩ በውኃ ጀርባ ላይ መራመድና መንሳፈፍ ይችላሉ፡፡
መጽሀፍ
ቅዱስ እንደሚለን ከአዳም የወረስነውን የሀጢያት ሸክም የሚሸከም አንድም ነብይ ወይም ካህን ከምድር ላይ ባለመገኘቱ እንደ ውኃ ሁሉ
ይህን ሀጢያት መሸከም የሚችል አንድያው የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን በቤተልሄም ተወልዶ፣በዮርጋኖስ ተጠምቆና በቀራኒዮ ተሰቅሎ
በሞት ጀርባ ላይ አንሳፎናል፡፡
6. ውኃ ህይወትን እንደሚሰጥ ሁሉ ይህወትን ይነጥቃል
ወኃ
በአግባቡ ሳንገለገልበትና ሳንከባከበው ስንቀር በውኃ ወለድ በሽታዎች፣ በመአበል፣በጎርፍና ሀሪኬይን በመሳሰሉት ነገሮች ያጠፋናል፡፡
የሰው
ልጆች እግዚሀብሄር አምላክ ካስቀመጠላቸው ህግ ሲወጡና የእግዚሀብሄርን ትዛዝ ባለማክበር ልበ ደንዳና ሲሆኑ አምላክ ውኃን እንደ
መቅጫ እንደሚጠቀምበት በግብጻውያን እና በኖህ ዘመን ሰዎች ታሪክ ተምረናል፡፡ ውኃ ለኖህና ቤተሰቦቹ እንዲሁም ለሙሴና ለእስራኤላውያን
በረከት እንደሆነው ሁሉ ለግብጻውያንና ለኖህ ዘመን ሰዎች መርገምት ሲሆንባቸው አይተናል፡፡
ውኃ
ለስላሳ ነገር ነው ነገር ግን ማንም ሊቆጣጠረውና ሊያቆመው አይችልም እግዚሀብሄርም በቃልኪዳኑና በምህረቱ ካልተያዘ ማንም ሊቆጣጠረው
ሆነ ሊያቆመው አይቻለውም፡፡
***
እነሆ
ጊዜ በኖረና ብዙ ባልኩ ነገር ግን «ተጠምቀ
ሰማያዊ በእደ መሬታዊ፤ ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ» የሚለው የዕለቱ ቀለም በሊቃውንቱ አንደበት በያሬዳዊ ዜማ ጎልቶ ይሰማኛል። ወንዱ በሆታ፤ ሴቱ በእልልታ፤ ካህኑ በሃሌታ ታቦተ ሕጉን አጅበው ሲጓዙ ይሰማኛልና ልቤ ጓጓ፡፡ የውኃ
ታምራዊ ተፈጥሮ በዚህ አያበቃም በሌላ ጊዜ እንደምመለስ ቃል እገባለው እስከዛው ይህን የእግዚሀብሄር መገለጫ የሆነ ውብ ተፈጥሮ
የጥምቀትን በአልን ምክንያት በማድረግ ወንዞችና ሀይቆቻችንን በመንከባከብ እናክብረው እላለው፡፡
አሸናፊ አበራ ነኝ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ