ዶ/ር ዐብይ የህመም ማስታገሻ ወይስ መድሀኒት?


ዶ/ር ዐብይ የህመም ማስታገሻ ወይስ መድሀኒት?
ዶ/ር ዐብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን “የጠቅላይ ሚንስቴራችን” ሆኖ፤ በደረቅ ወንበር ላይ ሳይሆን በልባችን ዙፋን፣ በጥቂቶችን አፍ ውስጥ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ከነገሰ ዛሬ 138 ቀናት ተቆጠሩ፡፡ በነዚህ ጥቂት ቀናት ውስጥ ግን አጀብ የሚያሰኙና ህልም የሚመስለ ወርቅ ጊዜያትን አብረንው አሳለፍን፡-
ዶ/ር ዐብይ እጁን አንስቶ ከማለባት ቀን ጀምሮ “የድሮ ስርአት ናፋቂ እንዳንባል፣ጠባብ ወይም ደግሞ ትምክተኛ የሚባል ታልጋ እንዳይለጠፍብን፣አሊም በግምገማ እንዳንፈረጅ ፈርተን (ለሆድ ለንጀራ) በአደባባይ መጥራት የተውነውን የምዬን ስም አገሪቷ እያሉ አገራችንን ባስረሱን ፊት ፋኖ ሆኖ ኢትዮጽያና ኢትዮጵያዊነትን አመሳጥሮ ጠርቶት ሁላችን በአደባባይ ኢትዮጵያ ብለን መጮህና እውነተኛውን መቀነቷን በግልጽ ከፍ ማድረግ ቻልን፡፡ አብይ በጥቂት ቀናት ውስጥ የጠፋችብንን ኢትዮጵያዊትን ሰጠን፡፡ ከሁሉ በላይ ፍቅርና አንድነታችንን መለሰልን፡፡
የሙያ ነጻነታቸውን “በልማታዊ ጋዜጠኝነት” ስም ተነጥቀው የካድሬ አፍ ሆነው ሲያደነቁሩን የነበሩ የአገር ውስጥ ሚዲያዎችንና ባለሙያዎችን ከእስራታቸው ፈቶልን፤ ዲሽና ኢሳት እያለን እንኳን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን አምነንን መመልከት ጀመርን፡፡ አምሳለ ክርስቶሱ ዐብይ ለአገራቸው ከገዥው ፖርቲ የተለየ ሀሳብ ስላለቸው ብቻ እንደ ይሁዳ ተቆጥረው እንደ ቃየል በየሜዳው ሲሳደዱ የነበሩ የተቃዋሚ ፖርቲ አመራርና አባላቶችን ስማቸውን ቀይሮ የኢትዮጰያ ምርጥ ተፎካካሪ አደረጋቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆናችንን ብቻ አክብሮ በግለሰብ ደረጃ የታመመውን እየጎበኝ፣ የተሰደደውን ፈልጐ እያመጣ፣ የታሰረውን እያስፈታ፣ ፍርድ የጐደለበትን ፍትህ እየሰጠ፣ የተበደለውን ይቅርታ እየጠየቀ ኢትዮጵያዊነት/ኢትዮጵያዊ ከማይታይና ከማይዳሰሰው ወይም ህልውና ከሌለው ዘር፣ጐሳና ቡድን በላይ እኔና እንቺ መሆናችንን አሳየን፡፡ አብይ በጲላጦስ አደባባይ በከሳሾቻችን ፊት ለፊት ወንጀለኛው በርባን እንደነበር በድፍረት በመመስከር ንጹህ ክርስቶስን ለፋሲካችን ፈታልን፡፡  
ዶ/ር ዐብይ በ138 ቀናት ብቻ ባቢሎናውያኑ ስንት ሌሊት የደከሙበትን የጥላቻ ግንብ (ትምህርት ቤት ወይም መንገድ የሚገነባ ሚሊዮን ብር ሳያባክን) በፍቅር የመደመር መዶሻና በይቅርታ በትሩ ብቻ ግንቡን ናደው፡፡ የኛ ሙሴ (የዮቶር ልጅ) የመደመር መዶሻው ሀይል ከኛ አልፎ በፍቅር በትሩ የኤርትራን የጥላቻ ባህር በመክፈል የኢትዮጵያና የኤርትራን ህዝቦች በደረቅ መሬት አሻግሮ ዳግም በፍቅር አስተቃቀፋቸው፡፡ ከሁሉ በላይ ዶ/ር ዐብይ ጠንክረን የምንማርበትን፣ ጠዋት ተነስተን ወደ ቢሮ የምንሄድበትን፣ የምንነግድበትን፣ ቤተሰብ መስርተን ልጅ ወልደን የምናሳድግበትን ተስፋ ሰጠን፡፡ አገር ሰጠን፡፡ ዐብይ መደመርና ይቅርታን ብሔራዊ መዝሙራችን አድርጐ ሁላችንን ግንብ አፍራሽና ድልድይ ገንቢ አደረገን፡፡

ዐብይ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይህን ሁሉ ማድረግ በመቻሉ ብቻ በጥቅም የተኮላሹ ካድሬዎች እንደ ፖሊዮ ከታቢ ቤት ለቤት እያንኳኩ ሳይቀሰቅሱን፣ በ1ለ5 “ጠርንፈው” በውይይትና በግምገማ ሳያደርቁን፣ ዘይትና ስኳር ኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤት ይከለክሉን ይሆን ብለን ሳንሰጋ እና ቲ-ሽርት በነጻ ሳይታደለን (በገንዘባችን ገዝተን) በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል በውጭ አገራትም ሳይቀር ለአብያችን እውነተኛ የድጋፍ ሰልፍ ወጥተናል፡፡
ይሁን እንጂ ዐብይና ለውጡ ለኛ ለኢትዮጵያን መድሃኒት ሳይሆን የህመም ማሰታገሻ ሆኖ እንዲቀር የሚጠሩ ግን አልጠፉም፡፡ አሁን አሁን በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚታዩ ስርአት አልበኝነቶች የደስታችን ማደብዘዣ መርዶዎች ሆነው፡፡ ለዚህ ግጭት መባባስ አላዋቂ የመደመር ጭፍን ደጋፊዎችና የነጻነት ሰካራሞች አስተዋጾ ቢኖርበትም ቀዳሚ ተጠርጣሪዎች ግን በዐብይ ወደ ስልጣን መምጣት የተነሳ ስልጣናቸው ከድቷቸው ኪሳቸው የቀለላባቸው ንዑሳን ከበርቴ አመራሮች፤ በፊት በኮንትሮባንድ ንግድ የደለቡ አሁን ጎተራቸው የደነገጠባቸው ፊውዳሎችና የጥቅም ተጋሪ ጀሌዎቻቸዉ እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ደገሞ ደርግ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴን መንግሥት አውርዶ የመሬት ለአራሹን አዋጅ ለማወጅ በተዘጋጀበት ወቅት ህዝቡን በጭሰኝነተ ሲበዘብዙ የቆዩና የፊውዳል ባላባቶች አዋጁ አስደንግጣቸው  ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ ሰው የማፈንና የመግደል እንዲሁም ብጥብጥ የማስነሳት ሙከራ ማድረጋቸውን ከታሪክ የምናገኘው ምስክርነት ነው፡፡
የኛ ዘመኖቹም “የቀን ጅቦች” (እኔ የደመና ጅቦች ስለምላቸው ነው በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ደረኩት) የኢትዮጵያ ህዝብ በስንት ትግልና ጸሎት ያገኘውን ድል ለመቀልበስና የታየውን የተስፋ ብርሃን ለማደብዘዝ ግጭትን ስፖንሰር ከማድረግ አልፈው ህዝቡን በተለይም ወጣቱን ስሜታዊ ለማድረግ እንደ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ያሉ የህዝብ ቁንጮዎችን እስከመግደል መሄዳቸው የዚሁ ታሪክ ቀጣዩ ክፍል ነው፡፡ቀደም ሲል በደቡብ ክልል (በሲዳማ በወላይታ፣በጉራጌ፣በከፋና በቤንች ማጂ) እንዲሁም በኦሮሚያና በሶማሌ አሁንም በኦሮሚያ (በባሌ ጐባና በደንቢ ደሎ፣በደቡብ (በጉጂና ጌዲኦ)፣በጅግጅጋ፣በምስራቅ ሐረርጌ፣በአዳማ፣በሻሸመኔ ተቀስቅሶ የነበረውና አሁንም ያለው ግጭት የቀን ጅቦች የጥቅም ትግል ማሳያቸው ናቸው፡፡
በጠቅላይ ሚንስትራችን ላይ የቦንብ ሙከራ ተቃቷል፣ የዳንጐቴ ስሚንቶ ፋብሪካ አመራሮች ተገድለዋል፣ ለመውለድ ወደ ሆሰፒታለ የምትሄድ ነፍሰ ጡር ህይወቷ በታጣቂዋች ተነጥቋል፣ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በጠራራ ፀሐይ ጆሮግንዱን በጥይት ተመቶ ሞቷል፣ ማረሚያ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ አብያተ ክርስትያናት ነደዋል፣ ካህናት እንደ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግረዋል፣ንጹሀን ዜጎች በጥይት ተቆልተው ሞተዋል፣ ወንድማችን በአውሬነት ጭካኔ እንደ ጴጥሮስ በአደባባይ ቁልቁል ተሰቅሎ ተገሏል በየቦታው ግማሽ በኦነግ ስም ሌላው በቄሮ ስም ሌላው በሱማሌ ልዩ ሀይል ሰም (ወይም የሱማሌ ልዩ ሀይል ራሱ) የሚነግዱ የታጠቁ ኃይሎች መሳሪያ ይዘርፋሉ፣ ሰዎትን አፍነው ይወስዳሉ፣የንፁሀን ነፍስ በከንቱ እንደዋዛ ይቀጥፋሉ፡፡ፈጻሚው ማንም ይሁን ማን መቆም ግን ይኖርበታል፡፡ ታዲያስ ይህን የሚያስቆምልን ማን ነው? ህዝቡ እኔን ጨምሮ “የፍትህና የህግ የበላይነት ያለህ” እያለ ነው::
ወጣቱ በግምትና በጥርጣሬ አንድ ግለሰብ ወይም ብሔር ላይ ጣት ከመጠቆም አልፎ እንደ ሻሸመኔው አይነት ዘግናኝ እርምጃ እየወሰደ የማያባራ ብጥብጥ ውስጥ ከመግባታችን በፊት መንግስት ለነዚህ ጥፋቶች ተጠርጣሪም ሆነ ተጠያቂ የሚያደርገው አካል ወይም ግለሰቦች ካሉ ለህዝቡ ማሳወቅና በአፋጣኝ አጣርቶ ተገቢውን ፍትህ መስጠት ይኖርበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ ለእርምጃ አለመቸኮላቸውና አስሮ ከማጣራት አጣርቶ ማሰር መፈለጋቸው ከዲሞክራሲያዊ መሪ የሚጠበቅ ስልጣኔ መሆኑንም አልካድኩም፡፡ እኔም ልክ እንደርሳቸው ሁሉ ለአንድ ጠማማ ዛፍ ጫካ መመንጠር አለበት የሚል ግብዝ አስተሳሰብ የለኝም፡፡ አይጥ አይጥ ብትሆንም እንኳን በእንጨት አናቷን ከመባሏ በፊት ከምጣዱ ላይ መውረዷን ማረጋገጥም ያስፈልጋል፡፡ አያቴ እንደምትለው አገር ተሰብራ ጦማችንን ከምናድር “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ”፡፡ ነገር ግን የደ/ር ዐብይ መንግሥት በፍጥነት ከጫካው መሀል የተደበቀውን ጠማማ ዛፍ ማንነትና እኩይ ድርጊቶቹን አጣርቶ ለህዝብ ሊያሳውቅና ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ ዶ/ር ዐብይና መንግስታቸው አይጧ ከምጣድ ወርዳ ጐሬዋ ከመደበቅዋ በፊት በጥንቃቄ ደፈርና ፈጠን ብሎ አይጧን በምናምን ይዞ ሊያነሷትና ፍትህ ሊሰጧት ይገባል፡፡ መንግስት አጉል መፍራትና መለሳለሱን አቁሞ የህግ የበላይነትን ማስጠበቅና ፍትህን ማረጋገጥ ካልቻለ በጊዜ ሂደት ሊፈጠር የሚችለው ጥፋት እጅክ የከፋ ይሆናል፡፡
ለዶ/ር ዐብይና እርሳቸው ለሚመሩት መንግሥት ሁሉ ነገሩን ሳይሰስት የሰጠው ህዝብ አሁን ላይ ከዶ/ር ዐብይና ከመንግስታቸው ጥበቃን ይፍልጋል፡፡ የአንድ መንግስት የመጀመሪያ ግዴታ ደግሞ ለህዝቡ አስተማማኝ ጥበቃ መስጠት መቻል ነው፡፡ ይህ እውን ሊሆን የሚችለው ደገሞ መንግስታችን ጠንከር ብሎ ህግና ስርአት ለማስፈን መቆም ሲችል ነው፡፡ ከሌሎች አገራት የውድቀት ታሪክ እንደምንረደው መንግስት ለዜጋው አስተማማኝ ጥበቃ ማድረግ ሲያቅተውና ህዝብ ፍትህን ሲራብ ህዝቡ እንደ ታሊባንና አይ ኤስ አይ ኤስ ያሉ ፅንፈኛና ፈላጭ ቆራጭ መንግስታትና አደረጃጀቶችን እስከ መምረጥ ሊያደርሰው እንደሚችል መገንዘበና አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይፈልጋል፡፡
የዶ/ር ዐብይ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ ከእርስ በርስ ግጭትና ከቀን ጅቦች ጥቃት መጠበቅ እንዲሁም በከንቱ ለሞቱት ኢትዮጵያውያን ደም ፍትህን መስጠት ካልቻለ ዐብይ መድሀኒት ሳይሆን የህመም ማስታገሻ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ ምክንያቱም በመንግስት እምነት ያጣ ህዝብ በተለይ ወጣቱ ልክ እንደ ሻሸመኔው በጥርጣሬ ያሰበው አካል ለይ እጁን ማንሳት የጀመረውን ከቀጠለበት የባስ አለመረጋጋትና ግጭት በአገሪቱ ውስጥ ሊነግስ ይችላልና ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመደመር ዘመቻችንን ለቀን ጅቦች ምርኮ ሊያደርገው የማይችልበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡
ክቡር ጠቀላይ ሚንስቴራችን ሆይ፡-  
መንግስት እንደ ህዝብ ጠባቂ ሁኖ ለማገልግል ነፃ የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት፣ ፍርድ ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች መገንባትና እንዲሁም መልካም የመንግስት አስተዳደርን ማስፈን የሚችሉ አቅም ያላቸው የመንግሥት ተሿሚዎችን መያዝ ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም የአገራችን የፍትህና የፀጥታ ስራ ለማጠናከር መጀመሪያ “በሬ ሰርቀውን ሲያበቁ” ከጐን ሆነው “በሬው እንዳይገኝ አቅጣጫ የሚያስቱ”ና መረጃ የሚሰውሩ የበሬ ሌባ አመራሮችንና ባለሙያዎችን በአፋጣኝ በማጥራት የፍትህና የፀጥታ ተቋማቱን አስተማማኝ ቁመና ላይ ማድረግ ይጠበቅቦታል፡፡
እውነት እውነት እለዎታለሁ ሁሉ ነገርዎት ተመችቶኝ ጠቅላይ ሚኒስቴሬ ብዮታለው፡፡ ከእርሰዎ የቀረን አንድ ነው የመደመር ጉዞዎ ላይ ፍትህና የህግ የበላይነትንም ይደምሩልን፡፡
                                                

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ከ “ተደምሬያለው!!” ባሻገር

ውኃ ይሰማል ጉድ በል አበሻ ውኃ ይሰማል አለች ፈረንጅ