ውኃ ይሰማል ጉድ በል አበሻ ውኃ ይሰማል አለች ፈረንጅ


ውኃ ይሰማል ጉድ በል አበሻ ውኃ ይሰማል አለች ፈረንጅ
አሸናፊ አበራ
ውድ የሸገር ታይምስ ቤተሰቦች እንደምን ሰንብታችኋል? የጥምቀትን በአልን በማሳበብ የጻፍኩትንውኃ ና እግዜር” የሚለውን ጽሁፌን ስደመድም የውኃን ተአምራዊ ተፈጥሮ ለመንገር እንደምመለስ ቃል ገብቼ በነበረው መሰረት ባለቅኔው በአጼ ቴዎድሮስ የምናብ አንደበት ውስጥ “ቃል የእምነት እዳ ነው…”ያለውን አክብሬ እነሆ ተመለስኩ፡፡
ውኃ መሰረታዊ የፊዚክስንም ሆነ የኬሚስትሪን ህግ አይጠብቅም ለምሳሌ ሌሎች ቁሶች ሙቀት ሲነካቸው Heat cause expansion በሚለው የፊዚክስ ህግ መሰረት ሞሎኪውሎቻቸው ይስፋፋሉ ውኃ ግን በተቃራኒው ሙቀት ሲነካው ይኮማተራል ወይም (contract) ያደርጋል በቅዝቃዜ ጊዜ ደግሞ ይስፋፋል፡፡ ከቅዝቃዜ ነጥብ በታች ወይም below freezing point የሌሎች ቁሶች መጠናቸው (density) ሲቀንስ የውኃ ግን ይጨምራል above freezing point ሲሆን መጠኑ (density) ይጨምራል ከቅዝቃዜ ነጥብ በላይ ወይም above freezing point ሲሆን ደግሞ ይቀንሳል፡፡ ውኃ ብቻ የመሬት ስበትን እና ከባቢያዊ ግፊትን ጥሶ በረዣዥም ዛፎች ቅርፊት ውስጥ እያቆራረጠ ሽቅብ እስከ ጫፍ ይወጣል፤ውኃ ብቻ ሲፈልግ ፈሳሽ ሲሻው ጠጣርና ጋዝ በመሆን በተለያ ቅርጽ ይገኛል፡፡ ውኃ ከሌሎች ፈሳሶች በበለጠ ወደ ውስጡ የሚገቡትን ጠጣር ነገሮች በፍጥነት ያሟሟል ሌላም ሌላም፡፡ ውኃ ለምን የተለየ ሆነ የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚችለው እራሱ ውኃ ብቻ ይመስላል ጠያቂው ሳይንስ እንኳን መልሱን አልደረሰበትምና፡፡
የዚህ እንቆቅልሽ ፍቺ ሳይገኝ ተመራማሪዎችን በጥፍር ያቆመ ሌላ ክስተት በደቡብ ምስራክ ኤዠያ ውስጥ ተከሰተ፡፡ ጊዜው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1995 ዓ.ም. ነበር፡፡ በአንድ  ወታደራዊ ቅጥር ውስጥ ጅምላ ጨራሽ የሆነ አዲስ የጦር መሳሪያ ለመፈብረክ የተሰባሰቡ ከፍተኛ ተመራማሪዎች ሚስጥራዊ ስብሰባ ይዘዋል፡፡ ስለመሳሪያው ባህሪና የመግደል ብቃት ሞቅ ያለ ውይይት ደርጋሉ፣ ድንገት ሁሉም ክፉኛ ታመሙና በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ተወሰዱ፡፡ ምርመራ ሲደረግላቸው በከፍተኛ የምግብ መመረዝ እንደ ተጠቁ ተረጋገጠ፡፡ የበሽታውን መንስኤ ለማጣራት ሲሞከር ተመራማሪዎቹ አንድ ላይ የተጠቀሙት የተጠቀሙት ነገር ቢኖር በስብሰባ ክፍሉ ውስጥ የቀረበላቸው የታሸገ ውኃ ብቻ እንደነበር ተረጋገጠ፡፡ የህክምና ባለሙያዎች ውኃውን ወስደው ሲመረምሩት ምንም አይነት ለሰውነት ጎጂ የሆነ መርዛማ ነግር አልተገኘበትም፡፡ የውኃው ኬሚካላዊ ጥንቅር (chemical composition) እንደማንኛውም ውኃ የሁለት እጅ ሀይድሮጅንና አንድ እጅ ኦክስጅን ውህድ (H2O) ነበር፡፡ በነገሩ ግራ የተጋቡት የህክምና ባለሙያዎች የህክምና ሪፖርቱን ሲጽፉ እንዲህ ተነበበ “Poisoned by an Ordinary Water” በተራ ውኃ አማካኘነት የመጣ መመረዝ፡፡     
ይህ ሁኔታ ለሀያ አመታት ያክል ለሳይንስ እንቆቅልሽ ሆኖ ቆይቶ በመጨረሻ ስለውኃ ተፈጥሮአዊ ባህሪ አዲስና አስደንጋጭ መላምት ይዞ ተመለሰ፡፡ ውኃ የማስታወስ ችሎታ አለው ወይም “Water Has a Memory” የሚል፡፡
ነገሩ እንዲ ነው ማንኛውም ወደ ውኃ የቀረበ ውጫዊ ወይም አካባቢያዊ አካል በውኃው ላይ የራሱን ማስታወሻ ያትማል፡፡ ይህ ማለት በመኖሪያ ቤታችን ውስጥ መብራት ስናበራና ስናጠፋ፣ቴሌቪዥንና ሙዚቃ ስንከፍትና ስንዘጋ፣ በአምሯችን ስናስብም ሆነ ቃላት አውጥተን ስንናገር በቤታችን ያለው የውኃ ሞሎኪውል አወቃቀር (chemical structure) ይህን ሁኔታ ተከትሎ ይለዋወጣል ማለት ነው፡፡ ውኃ ልክ እንደ ኮምፒተር ሁሉ መረጃዎችን በውኃ ሞሎኪውሎች አማካኝነት ተቀብሎ የመመዝገብ ችሎታ ስላለው የተፈጠረውን ነገር መዝግቦ ይይዛል፡፡ የውኃ ሞሎኪውሎች የማስታወስ ችሎታ እንደ አማርኛ ሆሄያት ወይም እንደ እንግሊዘኛ አልፋቤት በዝሩ የተደረደረ ሲሆን ማንኛውም ውጫዊ አካል እንዚህን ፊደላት ተጠቅሞ በውኃው ላይ ቃላት መመስረት ወይም አርፍተ ነገር መጻፍ ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ ግኝት ለዘመናት ሲታመን ስለውኃ ሲታመን የቆየውን እውነታ ማለትም ለውኃ ተፈጥሮአዊ ጠባይና ጤናማነት ወሳኙ የውኃው ኬሚካላዊ ጥንቅር (chemical composition) ወይም የሁለት እጅ ሀይድሮጅንና የአንድ እጅ ኦክስጅን ውህድ (H2O) መሆኑ የነበረ ሲሆን በዚህ ጥናት የተረጋገጠው ደግሞ ዋናው ነገር የውኃው ሞሎኪውሎች አወቃቀር ወይንም (chemical structure) መሆኑን ነው፡፡
ቀለል ባለ አገላለጽ እነዛ ጅምላ ጨራሽ የሆነ የጦር መሳሪያ ለመፈብረክ በሚስጢር ተሰብስበው የነበሩ ተመራማሪዎች በውኃ አማካኝነት ሊመረዙ የቻሉት ምንም እንኳን የቀረበላቸው ውኃ ኬሚካላዊ ጥንቅር እንደማንኛውም መደበኛ ውኃ (H2O) ቢሆንም በሚስጥራዊ የምርምር ክፍላቸው ውስጥ ፊታቸው በቀረበው ውኃ ፊት ስለመርዝና ስለሞት እያሰቡና እያወሩ ቆይተው እኩይ ቃላቶቻቸውና ሀሳቦቻቸው በውኃው ላይ ታትመው ውኃው ቃላትና ሀሳባቸውን ተከትሎ (ሰምቶ) የሞሎኪውሎቹን ኬሚካላዊ መዋቅር በመቀየር ወደ መርዝነት መቀየር በመቻሉ ነበር፡፡
ተመራማሪዎቹ ነገራቸውን የበለጠ ለማብራራት አንድ ክስተት የጠቅሳሉ፡፡ በ1981 ከሊቨርፑል ወደ ሳንፍራንሲስኮ ጉዞዋን በማድረግ ላይ የነበረች ሎራ የተሰኘች ግዙፍ መርከብ ለሶስት ቀናት ያህል በሰላም ስትጓዝ ቆይታ ድንገት በተነሳ እሳት ከባሀር ላይ እንዳለች ወደ አመድነት ስትቀየር የመርከቢቱን ካፒቴን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሰራተኞች በነብስ አድን ጀልባዎች አማካኝነት ማምለጥ ቻሉ፡፡ ከሳትና ከመስመጥ ይትረፉ እንጂ ከውኃ ጥም ስቃይግን ማምለጥ አልተቻላቸውም፡፡ ጨዋማውን የባህር ውኃ አይጠጡ ነገር በፍጥነት እንደሚገላቸው ያውቃሉ፡፡ ሶስት ድፍን ሳምንታት በባህር ላይ ተጉዘው ደረቅ መሬት ላይ በሰላም ሲደርሱ ይህን ያህል ቀናት ያለ ውኃ እንዴት መኖር እንደቻሉ ለተጠየቁት ጥያቄ የመርከቧ ካፒቴን እንዲህ ሲል ተናገረ “ሁላችንም በውኃ ጥም በደካከም ስንጀምር ጀልባችን የተንሳፈፈችበትን ጨዋማ የባህር ውኃ ቁልቁል እያየው ሰላምና መረጋጋት በሞላው መንፈስ በልቤ ደጋግሜ እንዲህ አልኩ፡- ይህ ውኃ ንጹህና አዲስ (Clean and Fresh Water) ውኃ ነው፤ ቀጥዬም ጀልባዋ ላይ ለተሳፈሩት ጓደኞቼ ስለ ባህሩ ውኃ እንዲሁ እንዲሉና እንዲያስቡ ነገርኳቸው፡፡ ከዛም ምንም ሳልጠራጠር አጎንብሼ የባህሩን ውኃ በመዳፌ ሞላውና ጠጣውት ንጹህና አዲስ ነበር አለ፡፡” ይህን ጉዳይ ኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ “Three Weeks out of water” በሚል ርዕስ በፊትለፊት ገጹ ይዞት ወጣ፡፡
አሁን ተመራማሪዎች ይህን አስገራሚ የውኃ ጠባየ ተፈጥሮ ለማረጋገጥ የተለያዩ የቤተ ሙከራ ምርምሮችን ማድግና ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ታሪካዊ ክስተቶችን ተመልሰው ማጥናት ጀምረዋል፡፡
የሰው ሀሳብ በውኃ ላይ ያለው ተጽኖ (Effects of thoughts on water)
በአንድ የምርምር ላብራቶሪ ተመራማሪዎች በጽዋ የተሞላ ውኃ ሰዎች ፊት አቀረቡና ሰዎቹ በተቻላቸው መጠን  ውኃው ፊት እንደ ፍቅር፣ ሰላም፣ ይቅርታና ምስጋና ያሉ መልካም ሀሳቦችን ብቻ በልባቸው እንዲያስቡ ጠየቁ፡፡ በተመሳሳይ ሌላ በጽዋ የተሞላ ውኃ ቀረበና እነዚሁ ሰዎች ከቅድሙ የተቃረኑ እንደ ጥላቻ፣ቅናት፣ንዴትና ሽንፈት የመሳሰሉ ክፉ ሀሳቦችን በውኃው ፊት እንዲያስቡ አደረጉ፡፡ በመቀጠል ሁለቱን የውኃ ጽዋዎች ላብራቶሪ በመውሰድ የውኃ ናሙናዎቸሁን ሲያዩ ፍጽም ልዩነት ነበራቸው፡፡ መልካም ሀሳብ ሲታሰብበት የነበረው ውኃ ክፉ ሀሳብ ሲታሰብበት ከነበረው ውኃ ጋር ሲነጻጸር ፈጽሞ የተረጋጋና የሀይል መጠኑም ከፍተኛ ነበር፡፡
ይህን እውነታ ከላብራቶሪ እንውጣና በአንድ ክስተት እናጉላው በመካከለኛው ጃፓን በቢዋ ሀይቅ ዙሪያ ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች ሀይቁ ላይ በቅሎ በነበረው አልጌ የተነሳ ሀይቁ በተፈጠረው መጥፎ ሽታ መማረራቸውን ለዘመናት ያቀርቡ ነበር፡፡ በ1999 በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሀይቁ ዙሪያ በመሰብሰብ ስለ አለም ሰላም ጸሎት አደረጉ ይህ በሆነ በወር ውስጥ አንድም ሰው ስለሀይቁ መጥፍ ሽታ ቅሬታ አላቀረበም፡፡ (የኛዎቹ የኢሬቻና የከተራ በአላት በውኃ አካሎቻችን ጤና ላይ ያለቸውን አውንታዊ አስተዋጾ ማን ያጥናልን ይሆን?)
ከዚህ የምንረዳው ነገር ይሉናል ተመራማሪዎቹ እያንዳንዳችን ውኃ ፊት ይዘን የምንቀርበው ውስጣዊ ሀሳብና ስሜት ውኃን ጥሩ ወይም መጥፎ ውኃ ማድረግ ከመቻሉም በላይ በተለይ ፍቅርና ምስጋና የውኃን ተፈጥሮአዊነት ከመጠበቅ በለጠ የሀይሉን መጠን ይጨምረዋል፡፡
የሁሉ ነገር መነሻ ሀሳብ ነው፡፡ በልባችን የሚመላሱ ሀሳቦችን በራሳች ህይወት እንዲሁም በዙሪያችን ባሉ ነገሮችን ላይ ሁሉ ተጽኖ ያሳድራሉ፡፡ መጥፎም ይሁን ጥሩ ነገር ቀድሞ በሀሳባችን ሳኖር በእጃችን ያለ ምንም ነገር የለም (As Within so without) እንዲሉ፡፡
የሰው ልጅ ሀሳብና ሌሎች ውጫዊ ድርጊቶች በውኃ ላይ ስለሚፈጥረው ተጽኖ ጥርጥር ላለው ሰው የጃፓናዊውን የውኃ ተመራማሪ የኢሞቶ ማሳኪን ስራ ማንሳቱ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ኢሞቶ ከሀያ አምስት አመታት በላይ ውኃ ላይ የተመራመረ ሲሆን ውኃ ለተለያዩ እንደ ቃላት፣ሙዚቃና ስዕልና የመሳሰሉ ውጫዊ ነገሮች ሲጋለጥ የሚያመጣውን የሞሎኪውሎች አወቃቀር ለውጥ የውኃ ቅንጣቶችን አቀዝቅዞ በፎቶግራፍ በማየት (documented molecular changes in water by freezing droplets of water and then examining them under a dark field microscope with photographic capabilities) አስደናቂውንና “ground breaking research” የሚል ማቆላመጫ የተሰጠውን የምርምር ስራ እንደሚከተለው ማከናወን ቻለ፡፡
ቃላት
ኢሞቶ ሶስት ጠርሙሶችን በውኃ ከሞላቸው በኋላ ሩዝ ዘፈዘፈባቸው፡፡ በየቀኑ ለአንድ ወር ያለማቋረጥ እየተመላለሰ ለመጀመሪያው ጠርሙስ በጃፓን ጨዋነት ገወገቡ ተጎንብሶ አመሰግናለሁ “Thank You” ይለዋል፣ ሁለተኛውን ጠርሙስ ደግሞ ደደብ ወይንም “You Idiot” ብሎ ይሰድበዋል፣ ሶስተኛውን ጠርሙስ ግን ደግም ክፉም ሳይናገረው ፈጽሞ ንቆ ይተወዋል ወይም “ignore” ያደርገዋል፡፡ ከወር በኋላ የሚመሰገን ውኃ ውስጥ ተዘፍዝፎ የቆየው ሩዝ በደንብ ተብላልቶና ውብ መአዛ አምጥቶ ሲገኝ፣ በሚሰደበው ውኃ የተዘፈዘፈው ሩዝ ጠቁሮና ገምቶ ነበር፣ የተናቀ ውኃ ውስጥ ተዘፍዝፎ የነበረው ሩዝ በበኩሉ ፈጽሞ መሻገትና መበስበስ ጀምሮ ተገኘ፡፡
እዚህ ጋር ልብ በሉልኝ ስንወለድ እስከ 90 በመቶ የሚሆነው የሰውነት ክፍላችን ውኃ ነው፣ እየጎለመስን ስንመጣ ወደ 70 በመቶ ይደርስና በመጨረሻዎቹ የእድሜ ጊዜያችን 50 በመቶ ይደርሳል፡፡ 85 በመቶ የሚሆነው የአእምሯችን ክፍልም ውኃ ነው፡፡ በግርድፉ እኛ ውኃ ነን ማለት ነው፡፡ እናማ ስለራሳችሁ ለራሳችሁ ስራወሩም ሆነ ስለ ሌላሰው ስታወሩ ቃላት ምረጡ፡፡ ቃላት ሀይል አላቸው፡፡ አለም በቃል ነው የተፈጠረው፣ በቃል ሰውን ማነሳሳትም ሆነ ቅስሙን መስበር ይቻላል፣ በቃል ሰውን መፈወስ ወይም መግደል ይቻላል፣ በቃል ሞትን ወይም ህይወትን፣ መርገምትን ወይም በረከትን መጥራት ይቻላልና፡፡ ኢሞቶ ሲናገር በተለይ ልጆቻችሁን ስታናግሩ ስለምጥጠቀሙት ቃላት ተጠንቀቁ እንደ ሁለተኛው ሩስ ጠቁረው ለናንተም ለማህበረሰቡም መጥፎ እንዳሆኑ ልጆችን ፈጽሞ ሰነፍ፣ የሞተ፣ደደብ በመሳሰሉ አሉታዊ ቃላት አትጥራቸው፤ደግሞም እንደ ሶስተኛው ሩዝም ችላ አትበሏቸው በመረሳት ስሜት መደበት ውስጥ ገብተው ይደነዝዛሉ ይላል፡፡
ተመራማሪዎች የፀሎት የመፈወስ ሀይል በውኃችን ላይ የሚፈጠር የቃላት ሀይል መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ጨምረውም በመመገብ ወቅት የሚደረግ ፀሎት ሳይንሳዊ ጥቅም እንዳለው ሲረጋግጡ ምግብ አብዛኛው ክፍሉ ከውኃ የተሰራ በመሆኑን በማስታወስ ምግብ ከመመገባችን በፊት ስንፀልይ የምንናገረው የምስጋና ቃል ምግባችንን ጤነኛና ጣፋጭ ያደርገዋል ይላሉ፡፡ የኛ እናቶችና አባቶች ይህን ቀድመው ተረድተው ይሆን ምግብ እየተበላ አይወራም የሚሉን? ይህን ተረድተው ይሁን በመልካም ቃላት የተባረከውን ፀበል የኑሮ ጣጣ የሚያነጫንጨው ጎጆ ውስጥ እንዳናስገባ ሚከለክሉን? ለዚህ ይሆን እናቴ እቤት ያዘጋጀችው ምግብ ቤተክርስቲያን ግቢ ሄዶ ስበላው የሚጣፍጠኝ ወይም የሰንበቴ ምግብ ሱስ የሆነብኝ?
ሙዚቃ  
ታምረኛው ውኃ የሚዚቃ ቀማሪው የባህ (Johann Sebastian Bach)፣ የክላሲካል ሙዚቃ ንጉሱ የሞዛርት (Wolfgangus Theophilus Mozart) እና የምትሀተኛው ፒያኒስት የቬትሆቨን (Ludwig van Beethoven) ለስላሳ ሙዚቃዎች ተከፈቱና ሰማ፡፡ እንዲሁም ጆሮ ጠልዝ የሆኑ የሮክ ስልት ያላቸው ሙዚቃዎችም ተከፈቱለትና ሰማ፡፡ ከሁለቱም የውኃ ቅንጣቶች ተወስደው በውኃ ተመራማሪው ኢሞቶ ላብራቶሪ ውስጥ ሲታዬ ለስላሳ ሙዚቃ የሰማው ውኃ አስደናቂ ሀይልና ብርሀን የነበረው ሲሆን ጠንካራ ሮክ የሰማው ውኃ ደግሞ በተቃራኒው ጨልሟል፡፡ ለዚህ አይመስላቹም አንዳንድ ዘፈኖች በሙዚቃቸው ንዴትና ጭንቀት ፈጥረው ጩህ ጩህ በረህ ጥፋ ጥፋ ሲያሰኙንና ዘፈኑ በያዘው ግጥም አማካኝነት በሚነገሩ ቃላቶች ድብርትና ሀዘን ለቀው ሲያኮራምቱን ሌሎች ዘፈኞች ደግሞ መንፈሳችንን አለሳልሰው እረፍትና እፎይታ ሚለግሱን?
ተመራማሪዎች መለስ ብለው ሲያዩ በአንድም የክላስካል ኮንሰርት ላይ እረብሻና ብጥብጥ ተነስቶ እንደማያቅ አረጋግጠዋል፡፡ (እህ እህ እናተ የእግርካስ ፌደሬሽን ሰዎች አጥር ከማጠር በተጨማሪ በየካምቦሎጆ የሚከፈቱና ደጋፊው የሚዘምራቸውን ዘፈኞች ብታጠኑ እኮ ብጥብጡን መቀነስ ትችሉ ይሆናል) በእርግዝና ወቅት የሚሰማ ለስላሳ ሙዚቃ የጽንሱን እድገት ያፋጥናል የልብ ምቱንም ያሻሽላል፡፡ ለስላሳ ሙዚቃ የተክሎችን እድገትም አትክልት እድገትንም ያፋጥናል፣ሀይማኖታዊ ዝማሬዎች፣ ቅዳሴና አዛን ምመኑን የመፈወስና መንፈስ የማረጋጋት ሀይል አላቸው፡፡ ጎበዝ የምንሰማውን አለማዊ ዘፈንም ሆነ መንፈሳዊ መዝሙር በመምረጥ ገንዘባችንን ብቻ ሳይሆን ውኃችንንም ከብክነትና ከብክለት እንከላከል፡፡
የታዋቂ ሰዎች ስም
እንደተለመደው ውኃ ቀርቦ ሰዎች የታዋቅ ሰዎችን ስም በፊቱ እንዲጠሩ ተደረገ አንዳንዶች ማዘር ቴሬዛና ማህተመ ጋንዲ የመሳሰሉ በጎ ሰዎችን ሲጠሩ ሎሎች ደግሞ የነሂትለርን ስም ጠሩ፡፡ ታማረኛው ውኃ በበጎ ሰዎች ስም መጠራት ምክንያት ሲፈግና በሀይል ሲሞላ በክፉዎቹ ሰዎች ስም ምክንያት ደግሞ ፈጽሞ አኩርፎ ተገኘ፡፡ ልብ በሉ ውኃው ሂትለርና ማዘር ቴሬዛን በአካልም በታሪክም አያውቃቸውም ግና ሰዎቹ እነዚህ ስሞች ሲጠሩ የሚኖራቸው የውስጥ  ስሜት ግን ተጋብቶበት ይቀያየራል፡፡ በአምላክ ስም፣ በመላክት ስም፣ በቅዱሳን ስም እንዲሁም በደግና በበጎ አድራጊዎች ስም ውኃችንን ማካም ሆነ እራሳችንን ማከም እንችላለን ማለት ነው፡፡ 
እንደው የእኛን አገር መሪዎች ስም እየጠራችሁ ውኃው ምን እንደሚመስል ለማየት አልጓጓቹም? ገቢያውን የሞሉት የታሸጉ ውኃዎች መጠሪያ ስምስ አላሳሰባችሁም?
ስዕል (Picture)
ታምረኛው ውኃ ስዕል እንደሚለይና የስዕሉም አይነት ውኃዊ ላይ ተጽኖ ማሳደር እንደሚችል ኢሞቶ አረጋግጧል፡፡ ውኃ የዶልፊን፣ የዝሆንና የልብ ቅርጽ የመሳሰሉ ስዕሎችን ይወዳል፡፡ እነዚህ ስዕሎች ከውኃው እቃ ላይ ሲለጠፉ ወይም ባቅራቢያው ሲኖሩ የውኃው ተፈጥሯዊ ሀይል ከመጨመሩ ሌላ የውኃው ሞሎኪውሎች የስዕሉን ቅርጽ ኮርጀው ተገኝተዋል፡፡
የቤት ስራ፡- እባካችሁ የውኃ ጆግና ብርጭቆዎቻችሁ ላይ ያሉትን ስዕላት አንዴ አስተውሉ? ልጆች ትምህርት ቤት ይዞው የሚሄዱት የውኃ ኮዳ ላይ ያለውን ስዕልስ አጢነዋል? ውኃ አምራቾች ማሸጊያው ላይ ስለምትለጥፉት ፎቶና ስዕል እባካችሁ ትኩረት ስጡ፡፡ ለዚህ ይሆን እንዴ ሀይማኖታዊ ስዕላቶችን የሚጠቀሙት?
ድሮ ውኃ የምንጠጣበት ባለአበባው ብርጭቆ ናፈቀኝ፡፡ 
የቧንቡዋ ውኃ
እስቲ በየቤታችን ስለሚደርሰው የቧንቡዋ ውኃ ደግሞ ተመራማሪዎች የደረሱበትን ድምዳሜ ልንገራችሁ፡፡ የቧንቡዋ ውኃ እቤታችን ከመድረሱ በፊት በተዘረጋ ትቦ ውስጥ ረዥም ኪሎ ሜትሮችን ይጓዛል፡፡ እነዚህ ትቦዎች ደግሞ ቅጥያና ጥምዝምዝነት ስለሚበዛቸው ውኃው በጉዞው አያሌ ጊዜ እየተገጫጨ ይጠመዛዘዛል፡፡ ከዚህ በፊት ደግሞ በኬሚካል የታገዘ ጠንካራ የማጣራት ሂደቶችን እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡ ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት እነዚህ ሂደቶች የውኃው ሞሎኪውሎች እንዲሰባበሩና ውኃው ተፈጥሮአዊ ማንነቱን እንዲያጣ ያስገድዱታል፡፡  በቀላለል አገላለጽ የቧንቡዋ ውኃ እቤታችን ሲደርስ ፍጽም ሞቶ ሲሆን እቤት ካለ እንሰሳ ወይም ሰው ተጨማሪ ሀይልን ይወስዳል፡፡ ተመራማሪዎቹ ይህንን መላ ምት ለማረጋገጥ የተጠማ ውሻ አመጡና በሁለት እቃ ውኃ ቀድተው አቀረቡለት አንዱ የቧንቡዋ ሲሆን አንዱ ደግሞ ከተፈጥሮ ምንጭ የተቀዳ ውኃ ነበር፡፡ ውሻው የተፈጥሮን ሀይል በአፍንጫው የማሽተት ችሎታው ተጠቅሞ ሁለቱንም ውኃ ካሸተተ በኃላ ህይወት ያለውን ከተፈጥ ምንጭ የተቀዳውን ውኃ መርጦ ላፈው፡፡ እኛም እነ መቻልን ጠርተን የተፈጥሮ ውኃ ብለው ማስታወቂያ ከሚለፍፉ እሽግ ውኃዎች አንዱን ይዘን ከቧንቡዋ ውኃችች ጎን ቀድተን መቻልን ባስመረጥነውና ጉዳችን በታየ፡፡
እና ምን እናድርግ
እናም እላችኋለው ሆን ብለን በማወቅ እንደ ፍቅርና ምስጋና የመሳሰሉ ቃላቶችን በውኃ መጠጫና ማስቀመጫ እቃዎቻችን ላይ እንዲሁም እቤታችንና ስራ ቦታችን የሚገኙ ቧንቡዋዎች ላይ እንለጥፍ፡፡ ውኃ እወድሀለውና አመሰግንሀለሁ በሚል ቃላት አክብረን እንጠጣው፡፡ የእለት ሀሳባችን ፍቅርና ምስጋና በማድረግ ለአለም ውኃ ጤንነትን እናሳልፍ፡፡ እኛ ሁላችን አንድ ነን እኛን ከመላው አለም ጋር አንድ እንድንሆን የሚያገኛኘን አንድ ነገር ደግሞ ውኃ ነው ይህን ውኃ በመልካም ሀሳባችን የውስጣችንና የአለምን ሰላም መመለስ እንችላለን፡፡ አንስታይን “እግዚሀብሄር እንዴት እንደሚያስብ ባውቅ በተለይም የፈጠራቸውን ነገሮች እንዴት እንደፈጠራቸው ብረዳ ደስ ይለኛል አለ፡፡” እኔም አሸናፊ አበራ ደስ ይለኛል ነገር ግን እኔ አዚህ ምድር ላይ ያለውት ይህን ድንቅ የአለም ፍጥረት ለማወቅ ብቻ ሳይሆን በነፍሴ ተረድቼ ለማመስገንም ጭምር መሆኑን አምናለሁ፡፡ እንግዲህ ውኃቹን በፍቅርና በምስጋና አክማችሁ ታከሙ፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ከ “ተደምሬያለው!!” ባሻገር

ዶ/ር ዐብይ የህመም ማስታገሻ ወይስ መድሀኒት?