አሮጌ አዲስ አመት
**አሮጌ አዲስ አመት***
(አሸናፊ አበራ)
ተነሱ ‘አዲስ አመት’ መጥቷል፡-
ግድግዳ እንጠብ፣
ገላ እንታጠብ፣
ሰሀን እናለቅልቅ፡፡
ዶሮ እናባርር፣
በግ እንደራደር፣
በሬ እንዘርጥጥ፣
ቅርጫ እንቃረጥ፡፡
ተነሱ ‘አዲስ አመት’ መጥቷል፡-
እንሶስላ እንሙቅ፣
ከበሮ እናሙቅ፣
ሹሩባ እናጥብቅ፣
ሙሬ እንታጠቅ፡፡
ድፎ ዳቦ እንድፋ፣
ችቦ እናቀጣጥል፣
እንጉርጉሮ ገባሽ፣
ብለን እንጨፍር፡፡
ተነሱ ‘አዲስ አመት’ መጥቷል፡-
ቄጤማ እነስንስ፣
ሉባንጃ እናጢስ፣
ፈንድሻ እንበትን፣
እንግጭ እንጎንጉን፡፡
ፌጦ እንፈትፍት፣
ስጋ እንበልት፣
(አጥንት እንከትክት፣)
ቢራ እንገልብጥ፣
ጠላ እንጨልጥ፡፡
ተነሱ ‘አዲስ አመት’ መጥቷል፡-
ቃል እናሰማምር፣
ለለውጥ እንፎክር፣
በቃ በዚህ አመት፣
እያልን እንገደር፡፡
ለአሮጌ ልምዳችን፣
ለአሮጌ ሀሳባችን፣
አዲስ ቁጥር ሰጥተን፣
ደሞ እንጃጃል፡፡


አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ