ኢየሱስን ፍለጋ


ኢየሱስን ፍለጋ
ቅዳም ስኡር ነው፡፡ ነጻነትን በማያውቁ ነጻ ሕዝቦች የፋሲካ በአል ግርግር ከተማዋ የጥንቷንና የአርቧን ቀራኒዮ አደባባይ መስላለች፡፡
ኢየሱስን ለሆዱ፣ለስራ፣ለስልጣን፣ለትምህርት ወይም ለውበት ዲናር የለወጠ ይሁዳ፤ፍትህና ምህረትን ከንጹሀን ነጥቆ ለበርባን የሸጠ ሙሰኛ፤በቀያፋ ጊቢ የእሳት ሙቀት እጅ መንሻ ተታሎ የልብ ጓደኛውንና ምሎ የተገዘተለትን ትዳር የካደው እኩይ ጴጥሮስ፤ ስለተደረገላቸው ነገር ተመልሰው ማመስገን የተሳናቸው ዘጠኝ ለምጣሞች፣ለዘጠና ዘጠኙንም ሆነ ለአንዲቷ በግ ፍለጋ የማይወጡና የማይወርዱ ካህናት፣የአሳ መረባቸውን በወንጌል ያልተኩ ሰባኪያን፣ከየቀን የሱስ መቃብሩ ፈንቅሎ መውጣት ያቃተው ሱሰኛ፣ነጻነት ከመርግ የከበደው የሐይማኖት ባሪያ፣ በዘረኝነትና በጥላቻ በመከፋፈል ጨለማ መቃብር ውስጥ በከሰረ ፖለቲካዊ አመለካከቱ ተገንዞ የተኛ ሬሳ ፖለቲካኛ፣በነጻነት ከሚያገኙት መና ይልቅ በባርነት የሚሰጣቸውን የግብጽ በጢኽ፣ ኩራት፣ ቀይ ሽንኩርትና ነጭ ሽንኩርት የሚናፍቁ ማጅራተ ደንዳኖችበጸጸትና በትዝታ ተጠቅልለው በትናንት ባርነት ውስጥ የሚያንቀላፉ ትዝተኞችና ቂመኞች፣ እንዲሁም በጥፋቴም ሆነ ያለጥፋ [1]የድሀ ልጅ ድሀ ያድርቆ ለባሽ፣ ያጥንተ ሰባራ የብረት ጠባሽ፣ ብሎ የሰደበኝ የሸማ ዘርጊ ልጅ ዲሪቶ ለባሽ ያ ትህትና የለሹ የክብሬ አሳናሽ ፍያታዊ ዘፀጋ እንኳን ፋሲካን ለማክበር በሚል ልማድ ግድግዳ በማጠብ፣ገላ በመታጠብ፣ቡቱቶ በመጨፈቅ፣ሰሀን በማለቅለቅ፣ዶሮ በማባረርና በግ በመደራደር እንዲሁም ድፎ በመድፋት፣ችቦ በማቃጠልና ቢራ በመጨለጥ እንደተዋከቡ በአሮጌ ሀሳባቸውና ተግባራቸው ተገንዘው በአዲስ መቃብር እንደተቀበሩና የቁም ሞታቸውን ድል ነስተው መነሳት እንደተሳናቸው አዲሱን ትንሳዬ እንደወትሮው ለመቀበል ይጃጃላሉ፡፡
***
ሰውዬው ልክ እንደ ነዌ ባለጸጋ ነው፡፡ የስጋውን ፍቃድ ሁሉ ማድረግ ይችላል፡፡ በዚህ የፋሲካ ዋዜማ ግን ያለ ወትሮው ሁሉ ሲኖረው ምንም እንደሌለው ባዶነት ተሰምቶታል፡፡ ህይወቱ ጨው እንደጎደለው ክሽን የፋሲካ ሌሊት ዶሮ የሆነ ጣ’ም ጎሏታል፡፡ መንፈሱ ከሰርቆ አደሮች (አመሰግናለው ዳኒ) መንፈስ በታች ወርዷል፤ የገንዘብ ባለጸጋነቱ ፈጽሞ የመንፈስ ባለጸግነትን ሊገዛለት አልቻለም፡፡
ሌቦች ሊሰርቁት ከሚችሉት ከዚህ ምድራዊ ሀብት የማከማቸት ፈተና የባከነች ሩሁን የሚሳርፍለት አንዳች አዲስ ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ በአንድ አጋጣሚ የተዋወቀው ክርስቲያን (ሰውየው እራሱን በሚጠራበት ቃል ነው) ሰው “ስሙ ብቻውን የጦለገ መንፈስን እንደ ሜዳ ሳር የሚያለመልም፣ በቃሉ ትዕዛዝ የተከዘ ልቦናን በሺህ የደስታ ዘፈኖች የሚሞላ፣ ሸክማችው የከበደ ሰዎችን ኑ! ብሎ በእቅፉ የሚያሳርፍ፣ የሞትን አፍ ድል የነሳ፣ ሁልጊዜ አዲስ የሆነ ኢየሱስ የሚባል ትሁት አገልጋይ አለ” ብሎ የነገረው ትዝ አለው፡፡ ባለጸጋው ይህን ኢየሱስን የሚሉትን ነጻነት ሊገናኘው ቸኩሎ ለትንሳኤ ልዩ ዝግጅት አለን ወደሚል አንድ አዳራሽ አመራ፡፡
***
አዳራሹ በስጋ ለባሽ ሰው ሞልቷል፡፡ ሰባኪው ከወዲያ ወዲህ እየተንጎራደደ እንዲህ ሲል ይጮሃል፡ “ኢየሱስ ትንሳኤ ነው፣ኢየሱስ ነጻነትና እድሳት ነው፡፡ ዛሬ አንድ ሰው ከአሮጌ ህይወቱ ላይ እንደ ፊኒክስ አዲስ ሆኖ ይነሳል እሰቲ አሜን”
ባለጸጋው ከምዕመኑ ጋር አብሮ “አሜን !” ይላል፡፡
“በኢየሱስ ደም ዛሬ አንድ ሰው ከድህነት አይን ተጋርዳል፣ድህነት አይነካችሁም፡፡ አሜን?”
“አሜን !”
“የድህነት መንፈስ ባስቸኳይ ከህይወታችሁ እንዲወጣ አዝዣለሁ አሜን ነው?”
 “አሜን !”
“ዛሬ ከድህነት መቃብር የምትነሱበት በፋይናንስ የምትባረኩበት ፋሲካችሁ ነው:: አሜን ነው ወይ! በረዥሙ ይጮሀል ሰባኪው፡፡
“አሜን !” ምዕመናኑም በረዥሙ ጮኸው ይመልሱለታል፡፡
“እመኑኝ ከኔ አይደለም፣የትንሳኤው ጌታ ኢየሱስ እንዲህ ብሎኛል እያንዳንዳቹ ከንግዲህ በ’ግራችሁ አትሄዱም”
 “አሜን !”
“ከእንግዲህ ከናንተ መሀከል በኪራይ ቤት መቃብር ውስጥ ተረስቶ የሚበሰብስ አይኖርም፡፡ አሜን!”
“አሜን!” ህዝብ ይጮሀል፤ከድህነቱ መቃብር ከኢየሱስ ጋር አብሮ በመነሳት የፋሲካ ተስፋው በመንፈስ ጥልቅ ስሜትና እንባ ይጽናናል፡፡
***
ባለጸጋው አስቀድሞ ይህ ሁሉ የስጋ ፍሬ ተሰጥቶታልና ሁሉም አለው፡፡ የእርሱ መቃብር ድህነት ሳይሆን እርካታ ማጣት ነው፡፡ የእርሱ መቃብር ገንዘብ ሳይሆን ማካፈል ነው፡፡ እርሱ የተጠማው አስቀድሞ ያልፈለገውን የጽድቅ ውኃ ነበር፡፡ እናም ካዳራሹ በፍጥነት ወጥቶ ካንዲት ዊስኪ ቤት ባለጌ ወንበር ላይ ተቀመጠና ዊስኪ አሶርዶ የኩባ ሲጋሩን እያጤሰ የቤቱን ባለቤት ቆንጆዋን ወይዘሮ አሰጠራት፡፡
ወይዘሮዋ ንጉስ ማይደስ እጆቹን በተለቃለቀበት የፓክቶለስ ወንዝ የወርቅ ውሃ ፊቷን የተለቃለቀች የንጋት ፀሀይ መስላና በንግስት ቄንጥ ደርበብ ብላ እየተራመደች መታ፣ ሰውዬውን ስታየው ከንፈሮቿ የህጻን ልጅ ፈገግታ እንደጎረሱ አጠገቡ ደርሳ ቁጭ አለች፡፡ ብርጭቆ እንዲያመጡላት ሊያጨበጭብ አስፍቶ የከፈታቸውን እጆቹን ለቀም አርጋ ይዛ አስቆመችውና እርግት ባለ ድምጽ፡-
“አልጠጣም” አለችው፡፡
“ለምን?” አላት ቀልድ እየመሰለው እየፈገገ፡፡
“ነጻ ወጣሁ” አለችው የቀድሞ እርጋታዋ ከመላ አካሏ ላይ እንደሰፈፈባት፡፡
“Indeed! አምሮብሻል መላ ሁኔታሽ ላይ የማልገልጸው አንዳች እንግዳ ለውጥ አያለሁ፤ምን ተገኝ ባክሽ?” አላት፡፡
“የሆነ ‘ለት ይዞኝ ያደረ አንድ ሰው ሲፈራ ሲቸኩል ጠዋት ሲሄድ ማታ ይዞት የገባውን ጥቁር የቆዳ ቦርሳ ከመኝታ ቤቴ እረስቶት ውልቅ አለ፡፡ ይመለስ ይሆናል ብዬ ምንም ሳልነካ እንደተቀመጠ ለብዙ ቀናት ጠበኩት፡፡ ሰውየው የውሃ ሽታ ሲሆን አንድ ጠዋት ቦርሳውን ከፍቼ ሳየው ጥቁር የሰባኪ ቀሚስ፣ነጭ ነጠላ፣በረዥም ሰንሰለት የታሰረ መስቀል፣መጽሐፍ ቅዱስና ቁጥርና በቀይ የተሰመሩ ዓረፍተ ነገሮች የበዙበት አጀንዳ በውስጡ ነበር፡፡ እርቃኔን በተጋደምኩበት ምን እንደገፋኝ ሳላውቅ ስፈራ ስቸር እጄ የመራኝ ስፍራ ላይ መጽሐፍ ቅዱሱን ከፍቼ አንዲት ምዕራፍ አነበብኩ፡፡ በዛች ቅጽበት ኢየሱስ ከሚባል ሰው ጋር ፍቅር ያዘኝ ተሸነፍኩለት፤በቀንም በሌሊትም ከርሱ ጋር መሆንን ተመኘው፣ ተቀብሎ ሙሽራው አደረገኝ፡፡” ብላ አይኖቿ በእንባ ተሞልተው ከንፈሮቿ እየተንቀጠቀጡ አላሶራ ስላሏት ዝም አለች፡፡
ባለጸጋው ባፉ ሳበውን የሲጋራ ጢስ ወደ ሳንባው ሳያስገባ ከሳቁጋር ወደውጭ እየበተነ አፉን ወደ ወይዘሮዋ ጆሮ አስጠግቶ “ዛሬ እኔ እራሴ ኢየሱስን ልገኛኘው ወድጄ መኖሪያ ቤቱ ድረስ ሄጄ ነበር፣ ነገር ግን ኢየሱስ የሚሰጠኝን ቀድሜ በራሴ ማግኘት መቻሌን አረጋግጬ ተመለስኩ:: ኢየሱስ የሚሰጥሽን ሀብት፣ ቤትና መኪና እኔ ልሰጥሽ እችላለው፡፡” አላት በሚያፌዝ ድምጽ፡፡
“ይህንማ እኔም ገላዬን ሸጬ አግንቼዋለሁ” አለችው፡፡
ባለጸጋው “ኢየሱስን ታዲያ ሌላ ለምን ትፈልጊዋለሽ? ኢየሱስ ሌላ ምን ሊሰጥሽ ይችላል?“ ሲል ሳይጨርስ አቋረጠቸውና፡-
“የኔ ብቸኝነት ይሁን የቃሉ ሀይል ምን ወደ መጽሐፉ እንደ ሳበኝ ምክንያቱን አላውቅም፡፡ እስከ አሁንም ድረስም አላውቅም፡፡ ብቻ አንድ ጠዋት የሌሊት እንግዳዬን አሰናብቼ በድካም በተጋደምኩበት መጽሐፍ ቅዱሱን ከፍቼ ማንበብ ስጀምር ማሪያም መቅደላዊት የምትባል ሴትን ሆንኩ፡፡” [2]ድምጹ ጆሮን አልፎ ልቦና ውስጥ የሚሰማ አንድ ሰው፡-
“እንዴት አደርሽ ማርያም? አለኝ”
“እንዴት አደርክ…” ብዬ ዝም አልኩ፡፡
ማን ብዬ እንድጠራው ስሙን እንኳን አላውቅም፡፡ ከዚህ በፊት ማንም ወንድ ተመልክቶኝ በማያቅበት ደግነትና ርህራሄ ተመለከተኝ፡፡ ርቃኔን ፊቱ የቆምኩ ያህል ሀፍረት ያዘኝ፡፡ ድምፄ እንደሰለለ፡-
እባክህ ልቤን አትያት ንጹህ አይደለችም አልኩት፡፡“
“ሁሌስ ንፁህ ያልሆነች ልብ አይደለች የምትስበኝ” አለኝ::
ያኔ ምን ማለቱ እንደሆነ አልገባኝም ነበር አሁን ግን ፈጽሜ ተረድቼዋለሁ፡፡“ይህን ሲል ህይወት ለሞት ሲናገር ይሰማኝ ነበር፡፡ ሞቼ እንደነበር ታወቀኝ፡፡ ከነፍሴ ጋር ፈጽሞ የተለያየሁ በመቃብር የተጣልኩ ምስኪን ሴት እንደነበርኩ ተሰማኝ፤የሁሉም ወንዶች ስሆን የማንም ነበርኩ፤ሸርሙጣዋ ሴት እያሉም ይጠሩኝ ነበር፤ የተረገምኩ ነበርኩ፡፡ ነገር ግን ቃሉ በልቦናዬ ሲገባ ጨለማው ማንነቴ እየፈዘዘ እየፈዘዘ ሲሄድና የመቃብር ድንጋዬ ከላዬላይ ሲንከባለል ታወቀኝ እናም ትንሳኤ የተገባኝ ማርያም ብቻ ሆንኩ፡፡” በጥልቅና አዲስ አይኖቹ እየተመለከተኝ እንዲህ አለኘ፡-
“ማርያም ብዙ ወዳጆች አሉሽ ነገር ግን እኔ ብቻዬን አፈቅርሻለሁ፤ሌሎች ወንዶች ለራሳቸው ሲሉ ይፈልጉሻል፣ እኔ ግን ለራስሽ ስል እፈልግሻለሁ፤ ሌሎች ወንዶች ስለሚታየው ውበትሽ ይወዱሻል፣ እኔ ግን በውስጥሽ ስላለው ስለማይታየው ነገር ሁሉ እወድሻለሁ አለኝ፡፡”
“እንባዬ በጉንጬ ላይ ወረደ፣ ይህ እንባ በጨለማ ህይወቴ መቃብር ሳለው እንዳነባሁት እንደ ቀድሞው አይነት እንባ ግን አልነበረም፡፡“ እናም ደግሞ አለኝ “ማርያም አትፍሪ እኔ ትሳኤሽም ህይወትሽም ነኝ፣እኔ ካለሁ በየ’ለቱ ከመቃብር መነሳትም ሆነ መለወጥ ይኖራል አለኝ፡፡“
“በዚያች ቀን ቃሉ ውስጤ ያለውን አሮጌ ጭራቅ አረደው፣ እናም ፋሲካ ሆነልኝ አዲስ ሴትም ሆንኩ ማርያም መቅደላዊት (ዘብሔረ- ኢትዮጵያ)፡፡“
ማርያም በደስታ እየተንሳፈፈች የእጁን ሲጋራ አስጥላ ባለጸጋውን ከተቀመጠበት የባለጌ ወንበር አስነስታ እጁን ይዛ እየመራችው ወደ ውጭ ወጡ፡፡ ባለጸጋው  እንደሷ ሞቱን ድል ለመንሳትና በኢየሱስ ትንሳኤ አዲስ ሆኖ ለመታደስ ኢየሱስን ፍለጋ በጉጉት ተከተላት፡፡
መልካም ፍለጋ ከዛም መነሳትና ፋሲካ ይሁንላችሁ፡፡


[1] ከዲያቆን ታደለ ሲገፉኝ ከተሰኘ የበገና መዝሙር የተወሰደ
[2] አንዳንድ የማርያም መቅደላዊት ንግግሮች ከካሊል ጅብራል jesus the son of man ከሚለው መጽሀፍ ተዛምዶና እንደወረደ ተተርጉሞ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ገጽ 15-17

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ከ “ተደምሬያለው!!” ባሻገር

ውኃ ይሰማል ጉድ በል አበሻ ውኃ ይሰማል አለች ፈረንጅ

ዶ/ር ዐብይ የህመም ማስታገሻ ወይስ መድሀኒት?