ፍቅር አደባባይ
ፍቅር
አደባባይ
መንፈሴ ዝቅ ሲል አዘወትሬ ከማደርጋቸው ነገሮች አንዱ የቻልኩትን
ያህል ልጅነቴን ማሰብ ነው፡፡ ልጅነቴን ለማሰብ ብዙ ጊዜ የምመርጠው ቦታ ደግሞ ሐራምቤ ሆቴልን ነው፡፡ ከሆቴሉ ሬስቶራንት ውስጥ
መስኮት ስር መሽጌ ቁልቁል አንባሳደር ላይ ስተክዝ ልጅነቴን ወለል ብሎ አየዋለሁ፡፡
****
ዛሬም እንደ ወትሮው ከሆቴሉ ተቀምጬ አምባሳደርን እያየሁ ከሰፊው
የህይወት ሁዳድ ላይ ሀሳብ ዘርቼ፣ ሀሳብ አጭጄ፣ የሀሳብ ነዶ እየከመርኩ ሀሳብ አበራያለሁ፡፡
****
ከሀሳቤ ላፍታ ስዘናጋ ከፖስታ ቤት አቅጣጫ ሆቴሉንና የመከላከያ
ግቢን እየታከኩ በቡድን በቡድን ሆነው ወደ
መስቀል አደባባይ የሚተሙ ሰዎች እንቅስቃሴ ቀልቤን ሳበው፡፡ ዛሬ የደመራ በአል ነው፡፡
****
"ንባብ ይገድላል
ትርጉም ግን ያድናል" ነውና ሀሳብ በነካው አእምሮዬ የደመራን ትርጉም ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ደመራ ደመራ… ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ
አደረገ፡፡ የግዕዝ ቃል ነው መቀላቀልን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሀድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትና ህብረትን ያመለክታል፡፡
በመስቀል ላይ በፈሰሰ ቅዱስ ደም የተነሳ የተገኘ ንጹህ ፍቅርና ፍጹም አንድነት፡፡
****
ተመልሼ የሚግተለተለውን
ህዝብ ተመለከትኩት፡፡ አብዛኛው ሰው ነጭ የአበሻ ልብስ ለብሷል፣ ወጣጦች መስቀልና የመስቀል ጥቅስ የታተመበት አንድ አይነት ከኔቴራ
(ቲሸርት) አድርገዋል፣ በአካላቸው የተለያዩ ቦታዎች ላይ መስቀል የተነቀሱ ጎረምሶችና ኮረዶች ንቅሳታቸውን የሚያጎላ አለባበስ ለብሰዋል፡፡
አንዳንዶች እየዘመሩ፣ ለሌች እየጨፈሩ፣ ሌሎች እያወጉ፣ ደግሞ ሌሎች እየተላፉ እንደ ወንዝ ወደ ደመራው አደባባይ ይፈሳሉ፡፡
****
ከአእምሮዬ ሳይሆን ከልቤ
የፈለቀ ጥያቄ መንፈሴን ወጠረው፡፡ ከዚህ ሁሉ ወፈ ሰማይ ህዝብ ስንቱ ይሆን የደመራ ትርጉም የገባው? ትርጉሙ ገብቶትስ ስንቱ ይሆን
መጀመሪያ ከራሱ አካላዊና ውስጣዊ ማንነት ጋር ደመራ አድርጎ ቀጥሎ ከቤተሰቡ፣ ከመሀበረሰቡ፣ ከአገር እንዲሁም ከመላው አለም ጋር
በአንድነት የሚኖርና ሱታፌን የተጎናጸፈ?
****
ደመራ መቀላቀል ሆኖ
ሳለ ለምን ሰርክ ጠንካራ የአንድነት ታሪካችንን እያጠለሸን ለመለያየታችን የቁርሾ ሰበብ ስንፈልግ እንውላለን? ደመራ መሰብሰብ ሆኖ
ሳለ ለምን እንደ ገለባ ለመበተን የንፋስ አፍንጫ ስናሸት እንውላለን? ደመራ መዋሀድ ሆኖ ሳለ ለምን ጸጉር ሰንጥቀን፣ አለት ሰልቅጠን፣
ዘይት ጨምቀን ከውሀ ጋር ለመቃቃር እንለፋለን?፡፡ በየቦታው ከሞኞችና ከየዋኾች አይን የተሰወረ አጥር አለ፡፡ ዩኒቨርሲቲ አጥር
አለ፣ መስሪያ ቤት አጥር አለ፣ ቤተክርስቲያን፣መስጂድ፣አዳራሽ አጥር አለ፡፡
****
በምንከተለው ሀይማኖት
የተነሳ ከወደድነው ሰው ይልቅ የጠላነው፣ ይቅርታ ካደረግንለት ይልቅ ቂም የያዝንበት፣ ከራራንለት የጨከንበት ሰው ይበልጣል፡፡ በዘር፣
በጎሳ እና ሌሎች ወደን ባልጠራናቸውና ፈልገን ባልመረጥናቸው ልዩነቶቻችን የተነሳ ካገዝነው ያደከምነው፣ ከሰበሰብነው የበተንነው
ያይላል፡፡
****
ታዲያስ ደመራው ወዴት አለ?
****
የጥያቄዎቼን ፍኖት ተከትሎ
“ጎልጎታ” የሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ
ደስታ ዘመን አይሽዬ የስነ ስቅለት ሥዕል ፊቴ እንደ መልስ ተከሰተ፡፡ ገብሬ በስደት እና በትምህርት ህይወት ባህር ማዶ በቆየበት ዘመን ነጮች
ለመላው ጥቁር ህዝብ ያላቸውን የጥላቻ ጥግ ለመግለጽ ረቂቅ የሆነውን እግዚሀብሄር ሳይቀር ነጭ ነው ብለው በመስበክ ተላላነታቸውን
ሲገልጹ በመመልከቱ ለዚህ ጠያፍ አስተሳሰብ መልስ ይሆን ዘንድ ክርስቶስን ነጭም፣ ጥቁርም፣ ጠይምም ሳያደርግ ድንቅ የፍቅር ቅኔን በብሩሹ ተቀኛና በደም ቀለም ብቻ ሳለው፡፡ ክርስቶስ ደም ብቻ ነው፡፡ የክርስቶስ
ደም በፍቅር ሀይል አስገዳጅነት ስለመላው የሰው ዘር የፈሰሰ ንጽህ የፍቅር ጅረት ነው፡፡ ይህ ፍቅር ሀይማኖት፣ ቀለም፣ ዘርና ጎሳ
የለውም፡፡
****
አሁንም አዘቅዝቄ ወደ መስቀል አደባባይ “ለደመራ” የሚጣደፈውን ህዝብ ቁልቁል ተመለከትኩት፡፡ ይህ ሰው
ለመስቀል ነው ወይስ በመስቀል ሰበብነት በደም ለተከፈለ ፍቅር ነው የሚንደረደረው? ይህ ሰው ከነገረ ስቅለቱ አካለ ክርስቶስን ነው
ወይስ ሀያል ፍቅሩን ነው ያስተዋለው? የማያባራ ጥያቄ፡፡
****
እመኑኝ ጥያቄዬ ሀይማኖት
የለውም፡፡ ጥያቄዬ ዘር የለውም፣ ጥያቄዬ የፖለቲካ ጎራ የለውም፣ ጥያቄዬ አገር የለውም፡፡ እውነተኛ ጥያቄ ከእውነተኛ መረዳት በቀር
መልስ እንኳን የለውም፡፡
****
መስቀሉ ላይ የክርስቶስን ግዙፍ አካል ብቻ የሚያይ ሰው ይሳሳታል፡፡ እይታው ውጫዊ
ብቻ ይሆንበትና ክርስቶስን አንዴ ጴንጤ፣ አንዴ ኦርቶዶክስ፣ አንዴ ነብይ፣ ሌላ ጊዜ ፈላስፋ፣ መምህር፣ መሲህ ወይም ኢማም እያደረገ
በከንቱ ሲከራከር ይኖራል፡፡ ለክርክሩ የመጨረሻ መልስ ስለማያገኝ በክርስቶስ የተነሳ ሌላውን በመናቅና በማጥላላት ይሰለጥናል፡፡
ስብከቱ ጥላቻና ስድብ፣ አስተምሮቱ ክርክር፣ መመላለሱ ልማድ፣ እውቀቱ ሽምደዳ ይሆንበታል፡፡
****
የሚያየው ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ብቻም ከሆነ ይሳሳታል፡፡ መስቀሉን ጌጥ
ወይም አርማ ያደርገውና ሙስሊም ወንድሙን ያገልበታል፣ ሌላውን አማኝ ሞኝ ብሎ ይዘብትበታል፣ ባስ ሲልም አርማውን ደረቱና ጋሻው
ላይ ስሎ ሰልፍ ይወጣል፡፡ ይህ ሰልፍ ቀላል ባለመሆኑ የብዙ ሰው ደም አፍስሷል፡፡
****
እንደ ገ/ክርስቶስ ዐይነ ልቦናው በጥበብ በርቶለት ደሙን ብቻ መመልከት የቻለ ግን እርሱ ፍቅርን ብቻ ይመለከታል፡፡ ደግሜ እለዋለው
በደሙ ላይ ዘር የለም፣ ጎሳ የለም፣ ጾታ የለም፣ ሀይማኖት የለም፡፡ ደሙ ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ሁሉን የሚያፈቅር፣ ሁሉን የሚያከብር፣
ሁሉን ይቅር የሚል አሸናፊ ፍቅር፡፡
****
ይህንን ፍቅር ያየና በዚህ ፍቅር
የተዳሰሰ ሰው የሚያሳድዱትን ይመርቃል፣ ለሚገሉት ምህረትን ይለምናል፣ የሚሸጡትን በርህራዬ አቅፎ ይስማል፣ የታናናሾቹን እግር በትህትና
አጎንብሶ ያጥባል፣ የተገለሉትን ይፈልጋል፣ ያዘኑትን ያጽናናል፣ ሰላምና አንድነትን ይሰብካል፡፡
****
ሐራምቤ ሆቴል ስመላለስ የተላመድኳት
አስተናጋጇ መሀሌት ወደ ተቀመጥኩበት መጥታ ግድግዳው ላይ የተሰቀለ ጽሁፍ እያነበበች ‘’እብዱ እንኳን ለብርሀነ መስቀሉ በሰላም
አደረሰህ’’ አለችኝና ሳቀች፡፡ አንድ ክረምት እዚህ ሆቴል የደራሲ አውግቸው ተረፈን ‘’እብዱ’’ መጽሀፍ ሳነብ ቆይቼ ጠረቤዛ ላይ
እረስቼው ሄድኩ፡፡ ይቺ አስተናጋጅ አንስታ አስቀመጠችና ከወራት በኋላ ስመለስ መጽሀፉን ሰጥታኝ በጨዋ ደንብ ‘’ሳላስፈቅድህ አላነብም
ብዬ አላነበብኩትም ርዕሱ ግን ስቦኛል’’ ብላ እንዳውሳት ጠየቀችኝ፡፡ ጨዋነቷ ገርሞኝ እድትወስደው ሰጠዋት፡፡ ስንግባባ እብዱ ብላ
ትጠራኝ ጀመር፡፡ ፈገግታዬን በፈገግታዋ ልክ መልሼ ‘’እንኳን አደረሰሽ አልኳት‘’ በሀሳብ መዋጤን አውቋ ጀርባዬን ነካ ነካ አርጋ
ፈገግታዋን መርቃልኝ ወደ ስራዋ ሄደች፡፡
****
መሀሌት ያነበበችውን ጽሁፍ ቀና ብዬ ተመለከትኩት ‘’እንኳን ለብርሀነ መስቀሉ በሰላም
አደረሳቸሁ!!!’’ ይላል ከጽሁፉ መሀል ለብርሀነ መስቀሉ የሚለውን መዝዤ አማዥገው ጀመር፡፡ የመስቀሉ ብርሀን አግኝቶናል ወይስ
በጨለማ ነን? ብርሀን ሀሴት ነው፣ መገለጥ ነው፣ ተስፋ ነው፣ ብርሀን ለሁሉም ነው፣ ብርሀን አንድነትና ፍቅር ነው፡፡ ብርሀን ያለው
እነዚህ ሁሉ አለው፤ ነገር ግን ብርሀን ያለው ጨለማ ሊኖረው አይችልም፡፡ ብርሀን በየትኛውም ጨለማ አይሸነፍም የድንቁርና፣ የጥላቻ፣
የሀይማኖት፣ የዘረኝነት፣ የመከፋፈልና ያለመደማመጥ ጨለማ ይህንን ብርሀን በፍጹም አይሸፍነውም፡፡ ይህ ብርሀን የመላው አዳም ዘርን
ጨለማ በአብረቅራቂ ጨረር የመላ ዘላለማዊ ፍቅር ነውና፡፡
****
ከውጪ በኩል መዝሙር ይሰማኛል
“እሰይ እልል በሉ ተገኘ መስቀሉ፣ እሰይ እልል በሉ ተገኘ መስቀሉ” የሚል፡፡ “አልተገኘም፣ መልሶ ተቀብሯል“ አልኩ በንዴት በጦፈ
ውስጣዊ ድምጽ፡፡ አዎ መስቀሉ በአይሁድ ቅንአት ለ300 ዓመታት በቆሻሻ ስር ተቀብሮ ቆይቶ ነበር፡፡ ዛሬስ? ለኔ መስቀሉ ዛሬም መልሶ ተቀብሯል አልተገኘም፡፡ ሀይማኖት የሚባል
የጥቅምና የፍርሀት አስተሳሰብ በሚረጨው የልዩነት፣ የጥላቻ፣ የአክራሪነት ቆሻሻ የተነሳ የመስቀሉ ታምር ተቀብሯል፡፡
****
መስቀሉ ከቁሻሻ ስር ተቆፍሮ
ሲወጣ የክርስቶስ መስቀል መሆኑ የታወቀው የተመሳቀለ እንጨት ስለሆነ ሳይሆን ድውያንን በመፈወሱ፣ እውራንን በማብራቱ፣ ጎባጣ በማቅናቱ
ነው፡፡ አንገታችን ላይ ያንጠለጠልነው፣ በእጃችን የያዝነው፣ በየልብሳችንና በየእቃዎቻችን ላይ የሳልነው፣ ገላችን ላይ የተነቀስነው
መስቀል የክርስቶስ መስቀል ከሆነ ቢያንስ በፍቅራችን፣ በአንድነታችንና በይቅርታ አድራጊነታችን ይታወቅ፡፡
****
የንግስት እሌኒ የደመራ ጢስ
ለመስቀሉ ሀይል እንደሰገደ፣ በንዴት ከላያችን ላይ የሚንቦገቦገው ትኩስ የዘረኝነት፣ የመከፋፈል፣ የአድመኝነት እና የጥላቻና እሳት
የፈጠረው ጢስ ለመስቀሉ ፍሬ ለሆነው ንጹህ ፍቅር ይስገድ፡፡ ልባችሁ በፍቅር የሰገደበት እርሱ ምልክታችሁ ነው፡፡
****
ቆይ እኛ ግን
ይህን እንዳናስተውል አዚም ያደረገብን ማነው?
****
ከሆቴሉ
ወጥቼ ወደ ፍቅር አደባባይ ሄድኩ፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ