.....አዲስ ዓመት የለም
.....አዲስ ዓመት የለም፡፡
ተፈጥሮ በፈጣሪዋ የተደነገገላትን
ህግጋት አክብራ ጨረቃ በመሬት መሬት ደግሞ በፀሀይ ዙሪያ የሚያደርጉትን የማያባራ ኡደት ሲፈጽሙ እኛ በበኩላችን መዓልቱን በፀሀይ
ሌቱን በጨረቃ አስልተን ለቀናቱ፣ ለወራቱና ለዓመታቱ ስያሜና ቁጥር እየሰጠን የዕለትና የዓመት ተግባራችንን አቅደን ወይም በዘፈቀደ
እየፈጸምን በምድር የተሰጠንን የኑሮ ጊዜ እንገፋለን፡፡
ጊዜ በመስፈርታት ተሸንሽኖ ከሳድሲት ሃምሲት፣ ከራብዒት
ሳልሲት፣ከካልዒት ኬክሮስ ከኬክሮስ ደግሞ ዕለታት እየተወለዱና ዕለታት አውደ ዕለትን፣ አውደ ወርህን፣ አውደ ዓመትን እየተኩና አውደ ዓመትም በበኩሉ ዓውደ አበቅቴ፣ዓውደ ፀሀይ፣አውደ ማሕተብ እየሆነ ግዙፉን
ዓውደ ቀመርን ለመደረብ ጊዜ እንደ ወንዝ ወደፊት ብቻ ይፈሳል፡፡
ይህ የማያባራ የዘመን ዶፍ በተደጋገመ
የመሬትና የጨረቃ ዙረት እራሱን ይደጋግማል፡፡ ምድርና ጨረቃ ኡደታቸውን ሲጨርሱ መልሰው ያንኑ ኡደታቸውን ይጀምሩና ከቅጽበት (ከካልዒት)
ኬክሮስ ከኬክሮስ ዕለታት መልሰው እየተወለዱ ግዙፎቹ ዓዕዋዳት ዳግም
ይወለዳሉ፤በዚህ ዙረት ውስጥ አዲስ ቁጥር እንጂ አዲስ ዕለት ወይም ዓመት የለም፡፡ በዘመን ጉዞ ላይ የሰው ልጅ አስተዋጾ ምንም
ነው፡፡
በዚህ የጊዜ ፍሰት ውስጥ አዲሱ የሰው
ልጅ አካልና መንፈስ ብቻ ነው፡፡ የአካል መታደስን በተመለከተ በየቀኑ 10-50 ትሪሊየን የሚደርሱ የሰውነታችን ሴሎች ሞተው በአዲስ
እየተተኩ አዲስ አካላዊ ማንነት ያላብሱናል፡፡ ይህም ደግሞ የተፈጥሮ ህግ ስለሆነ በሰው ይታገዝ ይሆናል እንጂ አይገዛም፡፡ እናም
ለሰው እውነተኛው አዲስ ነገር የመንፈስ አዲስነቱ ነው፡፡ የህይወቱ መነሻ የሆነውን የውስጥ ሀሳቡንና በመመርመር መረዳቱን ማስተካከል
ወይም መቀየር፣ በመረዳቱ አመለካከቱን የመለወጥና ህይወቱን (ስኬትና ውድቀቱን) የመቀየር የአዲስነት ስልጣን ነው፡፡
ዛሬ በውጭ በግልጽ የሚታየው እያንዳንዱ
የህወታችን ክፍል (ትምህርት፣ ስራ፣ ትዳር፣ ጓደኝነት፣ ሀብት፣ ድህነት…ስኬትም ይሁን ውድቀት) ትናንት የውስጥ ሀሳባችን ነበር፡፡
ሁሉ ነገር የሚጀምረው ከሀሳብ ነው፤የተደጋገመና ልቦናችንን የተቆጣጠረው ሀሳባችን በንግግርና በጽሁፍ ወደሚገለጥ ቃላት ይቀየራል፣የቃላት
ንግግራችን ሲደጋገም ወደ እንቅስቃሴ ይቀየርና ድርጊታችን ይሆናል፣ ድርጊታችን ሲደጋገም ጠባያችን ይሆናል ጠባያችን ወደ ስኬት ወይም
ውድቀት የሚመራን ፍጻሚያችን ነው፡፡ ስለዚህ ለጠባይ ለውጥ ዋናው የሀሳብ ወይም የአመለካከት፡፡
ሀሳብ ዘር ነው ልቦና የሚባል ሁዳድ
ላይ በየደቂቃው የሚዘራ ዘር፤ እኛ ደግሞ ይህንን ዘር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ስንዘራ የምንውል ገበሬዎች ነን፡፡ በሀሳቡ ስንዴ
የዘራ በህይወቱ ስንዴ ሲያጭድ በሀሳቡ እንክርዳድ የዘራ ደግሞ በህይወቱ እንክርዳድ ያጭዳል፡፡ እናም ዘወትር በጎ ለመናገርና በጎበጎውን
ለመተግበርና የስኬት ህይወት ለመኖር ዘወትር አውንታዊ ሀሳብ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
የሰው ልጅ ይህን ለማድረግ የአዲስ
ዓመትን መምጣት መጠበቅና በአዲስ ዓመት የለውጥ ልማድ ማመን አይጠበቅበትም፡፡ ሰው ከስጦታው ከአሁን (present) በቀር እርግጠኛ
የሚሆንበት ነገ እና በኋላ የሚባል ነገር የለውምና፡፡ እናም አሁኑኑ ድብቁ አእምሯችን ላይ ስለምንዘራው ሀሳብ እንጨነቅና አሉታዊ
ሀሳቦቻችንን በአውንታዊ ሀሳቦች እንተካው፣ በየደቂቃው አጥበቀን በጎ ሀሳቦችን ብቻ እናስብ፣ ስንናገር መልካም ዜናንና በረከትን
እንናገር፣ መልካምነታችን መለያ ጠባያችን እስኪሆን በተግባራችን ሁሌም ይገለጥ፤ እናም ያኔ በህይወታችን አዲስ ዕለትና አዲስ ስኬት ማየት እንጀምራለን፡፡
በአእምሮ የተጸነሰች ትንሽ የዘረኝነትን
ሀሳብ ናት አድጋ መለያየትና መሳደድ የምትፈጥረው ስለሆነም አሁኑኑ የዘረኝነት ሀሳብን በአዳሜነት (በአንድነት) ሀሳብ እንተካው፤
የድህነትንና የእጥረት ሀሳባችን ናት ፈጠራና ትጋታችንን ገላ ለማኝ ያደረገችን እናም ይህች እኩይ ሀሳብ አሁኑኑ በሀብትና በመትረፍረፍ
ሀሳብ ትቀየር፤ የድንቁርና ያለማወቅ ሀሳባችንን በእውቀት ፍለጋና በንባባብ ሀሳብ ይተካ፣ የጥላቻ ሀሳብ ለፍቅር ሀሳብ ቦታውን ያስረክብ…..፡፡
ለራሳችንም ሆነ ለሌላው ስንናገር
ተስፋን፣ፍቅርን፣አንድነትን፣መባረክንና ምስጋናን እንናገር፡፡ እርግማንና ወቀሳ፣ ትችትና ሀሜት፣ ስድብና የማማረር ቃል ከአንደበታችን
ይገደፉ፡፡ ሀሳብና አንደበታችን በፍጹም አልችልም፣ አይሳካም፣ አያልፍም፣አይለወጥም አይበል፡፡ ሁልጊዜም ስለሌላውም ሆነ ስለራሳችን
በረከትን ብቻ እናውጅ፡፡
አሉታዊ አመለካከቱን በአውንታዊ አመለካከት
የቀየረ ብቻ ዘመንን ይቀይራል (ያውም የገዛ እራሱን ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ያሉ ሰዎችና ሌሎች ፍጥረታትን ዘመን ሁሉ)፡፡ እናም
አዲስ ሀሳብ እንጂ አዲስ ዓመት የለም፡፡ ያለ አዲስ አመለካከት አዲስ ዓመት የለም፡፡
መልካም አውንታዊ አዲስ ሀሳብ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ