ዋናው አድሮ መገኘቱ ነው!!!


ዋናው አድሮ መገኘቱ ነው!!!
እማዬን ልጎበኝ ከመሸ ወደ አራት ኪሎ ጎራ አልኩ፡፡ እንደሁልጊዜው እድሜ፣ትምህርት፣ ትዳርና ስራ ያልሰጡንን ደግሞም የማይነጥቁንን ንፁህ ሳቅ ከእናቴና ከእህቶቼ ጋር ተሰብስበን ስንስቅ ቆይተን መላ ሰውነቴ ሳቅ እንደጎረሰ ተሰናብቻቸው ጉዞዬን ወደ ማደሪያዬ አደረኩ፡፡
ሽርሙጥናና ድንግልና፤ ስካርና ፀበልተኘነት፤ ሌብነትና ታማኝነት፤ ፀብና ፍቅር፤ ስድብና ውዳሴ፤እርግማንና ምርቃት፤ ጥንቆላና ሃይማኖት፤ ለቅሶና ጭፈራ፤ ረሀብና ቁንጣን፤ አለመማርና አስተዋይነት፤ብዙህነትና አንድነት፤ ድህነትና ለጋስነት ህይወትን ቀለል አድርጎ ከመኖር ፍልስፍና ጋር የተፈጥሮን የሁለትዮሽ ህግን (Law of Dualism) ተከትሎ የሚኖርበት ቦታ እንኳን ምን ቢያምርና በነዋሪዎቹ ምንኛ ቢናፈቅ ለዘላለም ቆሞ አንደማይቀር ህያው ምስክር የሆነችውን የአራት ኪሎን ፍራሰ-ገላ (መካነ-ትዝታ) አጽም አቋርጬ ታክሲ ልሳፈር ስላሴ ቤተክርስትያን ፊት ለፊት ቆምኩ፡፡
በመቆም ደቂቃዎችን ከገደልኩ በኋላ አንድ ቀባሪ ያጣ ሚኒ-ባስ ታክሲ መጥቶ ፊት ለፊቴ ቆመና የሆድ ዕቃው ተከፍቶ በቅድሚያ ረዳቱ ለጥቆም ሌሎች ተሳፋሪዎች ዱብ ዱብ እያሉ አስፋልቱ ላይ ተወለዱ፡፡ ረዳቱ በግራ ጉንጩ የወጠረውን የጫት ቡጢ በውኃ ወደሆዱ ከሰደደው በኋላ “መገናኛ መገኛኛ…ውስጥ መገናኛ” ብሎ ተጣራ፡፡
ፊቴ ያገኘውትን ሰው እየገፋው በሩጫ ወደ ታክሲው በር ተንደረደርኩ፡፡ በግፊ መሀል እንደቁርበት የደረቀ እጅ ድንገት ጀርባዬን እንደ እንሶስላ ሲፍቀኝ እሸሻለው ብዬ ወደ ፊት ስፈናጠር በሰማያዊ ጂንስ ሱሪ የተጠፈረ ቅርጸ መሶብ ቂጥ ስምጥ ሸለቆ አካፋይ ውስጥ ሙሉ አፍንጫዬ ተሰነቀረ፡፡ እንደምንም አፍንጫዬን ነቅዬ ደህንነቱን ለማረጋገጥ አየር ሳብ ሳብ ሳደርግ የአረቄ ሽታ አወደኝ፡፡ ደነገትኩ ግራ ገባኝ “አፍንጫዬ እውነቱን ነው ወይስ ማሽተቻው ተደበላለቀበት” ስል ከታክሲው ውስጥ መጠጥ አንደበቱን እንደ ህጻን ያጣፈጠለት ሰካራም በመውረድ ላይ ያሉትን ተሳፋሪዎች “የነገ ሰው ይበለን! ዋናው አድሮ መገኘቱ ነው!” እያለ ሲሸኛቸው ሰማውና አፍንጫዬንም ቂጡንም ከመጠርጠር አረፍኩ፡፡
በስላሴዎች ፀጋ ጀርባዬን እንደ እንሶስላ ከመፋቅና በቂጥ ታፍኖ ከመሞት ተርፌ ታክሲው ውስጥ በሰላም መዝለቅ ብችልም ክፉ እድሌ ከሚለፈልፈው ሰካራም ሰውዬ ጀርባ አስቀመጠኝ፡፡
ታክሲው ቤል-ኤር ጋር ሲደርስ ስሳፈር “ጫፍ ወራጅ ነኝ እለፍና ተቀመጥ” ብለው ወገቤን እንደ ማጭድ ያስጠመዘዙኝ ወፍራምና አስፈሪ ሰውዬ “ወራጅ አለ” አሉ፡፡ እረዳቱ በፍጥነት ዞር ካለ በኋላ መልሶ “ወራጅ አለ?” ሲል ጠየቀ፡፡ ወፍራሙ ሰው ጉንጫቸው እየተንቀጠቀጠ “ምን ይላል ይሄ ውርጋጥ እንደ ገደል ማሚቱ መልሰህ ካላስተጋባህ አትሰማም ወራጅ አለ ማለት ታዲያ ምን ማለት ኖሯል?” ሲሉ እረዳቱ ላይ ጥቁር ትላልቅ አይኖቻቸውን አፈጠጡበት፡፡
ሰካራሙ ሰውዬ ከስርቅታው ጋር እየታገለ ”አባባ አይቆጡ እረዳቱ ትክክል ነው በአደባባይ “ስልጣናችንን በገዛ ፍቃዳችን ለቀን ወርደናል“ ብለውን እልል ካስባሉን በኋላ ወዲው መልሰው ወደስልጣን የሚወጡ እፍርታም ፖለቲከኞች ባሉባት አገር እንዴት አንድ ተሳፋሪ ሊያውም አንድ ጊዜ ብቻ “ወራጅ አለ“ ስላለ መኪናን ያህል ነገር አምኖ ያስቁሞ? ቆይ እርሶም እንደ ፖለቲከኞቹ ሀሳብ ቀይረው አሎርድም ቢሉትስ?” አላቸው፡፡
ወፍራሙ ሰውዬ ለረዳቱ ያፈጠጡትን አይን የቅንድብ ከፍታ ብቻ ጨምረውበት ወደ ሰካራሙ ካዞሩት በኋላ “ሰውዬ ፖለቲካህን እዛው አታነካካኝ እኔ ፖለቲካ አላወራውም ወራጅ አለ ብቻ ነው ያልኩት” ሲሉ ጉንጫቸውን የበለጠ እያንቀጠቀጡ ተቆጡ፡፡
ሰካራሙ ሰውዬው ከመውረዳቸው በፊት ለመናገር እየተጣደፈና ቃላት አፉ ውስጥ ሟምተው እንዳይቀሩበት ታግሎ እያወጣቸው “ፖለቲካ ቢናገሩስ ምን አስፈራዎት? ከፈሩ እርሶ ዘመን አልቀየሩም ማለትነው? አሁን እኮ ዘመነ ንዑስን ሸኝተን ወደ ዘመነ ዐብይ በሰላም ተሸጋግረናል፡፡ በዚህ አዲስ ዘመን ያሻዎትን ያለምንም የግምገማ ስጋት በነጻነት መናገር ይችላሉ እኛም ያለምንንም ፍረጃና የጀርባ ጥናት እናዳምጦታለን፡፡ ለማንኛውም ዋናው ዛሬን በሙላት ኖረው ለነገ አድረው መገኘቶ ስለሆነ ደህና ይደሩ የነገሰው ይበለን” አላቸው፡፡
ወፍራሙ ሰውዬ የሆድእቃቸው ክብደት ከመሬት ስበትጋር አብሮ ቁልቁል ካስጎነበሳቸው በላይ ለሚኒባሱ ጣሪያ አደግድገው እየወረዱ በሚያምጥ ድምጽ “ምንአባቱንስና ይሄ ካቲካላም ደግሞ ላንተ ነገ መጣ ቀረ ምን ሊረባህናነው? ነግቶልህ ዳግም ካቲካላህን ልፈህ አፍህን ለመክፈት ነው ማደር እንዲህ ብርቅ የሆነብህ? ሰካራም!” ብለው እየተሳደቡ ወረዱ፡፡
ከተሳፋሪዎች መካከል ጥቂቶቻችን ሳቅን፡፡ ሰካራሙ ሰውዬ አንድ ጊዜ አጠገቡ ወደተቀመጠችው ቆንጆ ልጅ አንድ ጊዜ ወደኋላ እየዞረ “ቆይ እሺ ምን አጠፋው” ከተሳሳትኩ ንገሩኝና ልታረም ዋናው ማደርነው ወይስ ማደሪያ?” ብሎ ጥቂት ካፈጠጠብን በኋላ መለፍለፉን ቀጠለ “ለኔ መሬት ላይ ካርቶን አንጥፈህ እደር ወይም በኮንፎርት ኪንግ ሳይዝ አልጋ ላይ፤ በረንዳ ላይ እደር ቤት ውስጥ፤ ፍራሽላይ እደር ሶፋላይ፤ እስርቤት እደር ቤተ-መንግስት፣ሰርግ ቤት እደር ለቅሶ ቤት፤ ሸርሙጣ አቅፈህ እደር ድንግል ብቻ የትም እደር የትም ለኔ ዋናው የነገዋን አዲሲቷን ፀሀይ ለማየት በልብህ እየተመኝህ አድረህ ነገን መገኘትህ ብቻ ነው፡፡ ምንም አልም ምንም ተመኝ፣ ምንም እጣ ምንም አግኝ ዋናው ለዛሬ እጅ ሳትሰጥ የነገ ሰው ለመሆን ቆርጠህ ነገላይ መገኘትህ ነው፡፡ ዛሬን ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ በመኖርና ነገን እንደሚፈልጉት በተስፋ በመጠበቅ ውስጥ ሁሉ ነገር አለ” ሰካራሙ ዲስኩሩን ሳያበቃ ስርቅታ ምላሱን ገታው፡፡
በመሀሉ አጠገቡ የተቀመጠችው ቆንጆ ሴት ስልክ ተደወለላትና ስልኩ ውስጥ ለሚያወራት ሰው “ይኸው ደርሻለው እየመጣው ነው” ካለች በኋላ በጭንቀት ድምጽ “በናትህ በደንብ ንዳው” ስትል ሹፌሩን ተማጸነች፡፡ ሰካራሙ ሰውዬ ልጅቷ በችኮላ ስትቁነጠነጥ በአንክሮ ሲመለከታት ቆየና “የኔ’ህት የት ለመድረስነው ይሄ ሁሉ ጥድፊያና ችኮላሽ? ህይወት ባይቸኩሉባትም አጭር ነች፡፡ በአሉ ግርማ ከስብሀት ገብረእግዚሀብሄር ርዕስ እንደተዋሰ ሁሉ ከኔ አክስት ደግሞ ይህን ምክር መዋሱን ማን ያውቃል ማንም፡፡”
“ይኸውልሽ ቆንጅት ረጋ ብለሽ ኑሪ:: በመኖር ውስጥ የተጠላው እንደጥላ ያልፍና የተናፈቀው ይመጣል፤የጠፋው ይገኛል፣ ታላቁ ጥላቻ ወደፍቅር ይቀየራል፡፡ ለዚህ ምስክሩ ደግሞ ይሄ ዘመን ነው፡፡ አሁን ማን ይሙት ያ ያሳለፍነው ጨለማ ዘመን እንዲህ እንደ ክፉ ቅዠት ድንገት እልም ብሎ የሚያልፍ ይመስል ነበር? ከመሀከላችን የጠፋውን ፍቅርና ኢትዮጵያዊ አንድነት እንዲህ በቀላሉ ከተቀበረበት የዘርና የብሔርተኝነት የቁሻሻ ተራራ ስር ቆፍረው የሚያወጡ ቀና ልቦች ከደመና ጅቦች መሀል ይወጣሉ ብሎ ያሰበስ ነበር? በዚህ ጊዜ እንዲህ እንደ ቀልድ የኤርትራ ህዝብ “ተንኳሽ ጎረቤት” ከመባል ስድብ አልፎ ሰንደቅ አላማችንን በአደባባይ በማውለብለብ ወንድምነቱንና ፍቅሩን በለቅሶና በዘንባባ ዝንጣፊ ይገልጻል ያለስ ነበር? አየሽ ይህን የማቻል የሚመስል ነግር የቻሉ ሰዎች በጊዜው አገራቸውም ሆኑ እነሱ የትም ይሁኑ የትም በወቅታዊ ሁኔታ ሳይሸበሩና እጅ ሳይሰጡ ዛሬያቸውን በሙላት ኖረው ለዋናውና ለሚያልሙት ነገ መምጣት ተስፋ ሳይቆርጡ የሚተኙ ሰዎች ነበሩ ማለት ነው፡፡”  
እያለ በወኔ ሲናገር ከአፉ የሚረጨው አክታና አረፋ መሳይ ምራቅ ከፊሎቹ ከእኛ ፊት ላይ ሲረጩ ከፊሎቹ ደግሞ እጅብ ብሎ የበቀለው ከርዳዳ ሪዙ ላይ ተንጠልጥለው የከንፈሩን እንቅስቃሴን ተከትለው ዥዋዥዌ ይጫወቱ ነበር፡፡
ታክሲው ሾላ ገበያ ሲደርስ ሁለት ተሳፋሪዎች በቅጽበት ተቀዳድመው “ወራጅ! ወራጅ አለ” አሉ፡፡ ታክሲው ቆሞ ረዳቱ በር ሲከፈት ወራጅ ካሉት አንዱ ጎላማሳ ሰው ቀልጠፍ ብሎ እየወረደ በሰካራሙ ሰውዬ የድምጽ ቅላጼ “በሉ የነገሰው ይበለን ዋናው አድሮ መገኘትነው” ሲል ተሳፋሪው በሳቅ አስካካ፡፡
ሰካራው በተሳፋሪው ሳቅ እንደታጀበ “አዎ ወንድሜ ዋናው አድረህ መገኘትህ ነው የነገ ሰው ይበለን” በማለት ወራጆቹን ሸኝቷቸው ሲበቃ እውነት ይዞ መማለጃ መስጠት ስላልቻለና ወፍራም ዘመድ ስለሌለው ብቻ ፍትህ በተነፈገ ምስኪን ሰው ድምጽ “ቆይ ሰክራችኋል ወይስ ታማችኋል እሺ ለናንተ ዋናችሁ ምንድር ነው?  ዋናችን ዛሬን በሙላት መኖርና በተስፋ አድሮ ነገ መገኝት አይደለም ካላችሁ አሲዙኝና ደስታና ስኬቴን ብሉኝ ወይ እኔ ልብላችሁ፡፡
ይኸውላችሁ መገለጡ ይህ ነው ህይወታችሁን ስታደንቁ ሞት ይገባችኋል ልክ ሞት ሲገባችሁ ደግሞ ህይወትን የበለጠ ትረዳላችሁ፣ ህይወታችሁን ስትረዱ በእንዳንዷ ቀናችሁ ከህይወት የምትለምኑት ነገር ቢኖር በህይወት መኖርን ወይም አድሮ መገኘትን ብቻ ይሆናል ያን ጊዜ ጸሎታችሁ ሳይቀር ከልመናና ጭቅጭቅ ወደ ምስጋና ይቀየርና ሁሉ ይኖራችኋል፡፡” ሰካራሙ ሰውዬ ዳግም የካቲካላ ትንፋሹን አጠጥቶንና ምራቁን አርከፍክፎብን ሲያበቃ “ሰካራሞች ናችሁ” ብሌ ሰድቦን ትካዜ እንደገባው ሰው አቀርቅሮ ዝም አለ፡፡
ቅድም በቂጧ አፍና የመግደል ሙከራ ያደረገችብኝ ቂጣም ሴት “አይገርም ለሰካራም ሌላው ሰው ሁሉ እንደሱ የሰከረ መስሎ ነው ሚታየው ማለት ነው?” ስትል ጥግ ላይ አሮጌ ባርኔጣ አርጎ የተቀመጠ ወፍከልክል መሳይ ሰውዬ “ሰክረሽ አታውቂም ማለት ነው” ሲል በጥያቄ መለሰላት፡፡ ቂጣማ ሴትዮ “እውነት ሰክሬ አላውቅም” በማለት ከመለሰች በኋላ ደባሪ ሳቅ ስቃ ተሸኮረመመች፡፡ አሁን ወፍከልክሉ ሰውዬ በሌለው አንጀቱ ደፍሮ “እኔ ላስክርሻ?” ይላታል ብዬ ስጠብቅ ሰካራሙ ሰውዬ ቀድሞ “ውሸታም ሰክረሽ ታውቂለሽ” ሲል ቂጣሟ ሴትዮ ላይ አፈጠጠባትና እንዲህ አለ “ማንም በየጫካው የጠነሰሰውን የዘረንነት ጉሽ ጠላ ያለማጣሪያ ተግተሸ ስታበቂ የጥላቻና የመከፋፈል ስካር አልሰከርሽም? በየከተማው ለሆዳቸው ያደሩ ካድሬዎች የጠመቀውን የቋንቋና የዘር ጠጅ ተግተሸ ወንድምሽን ከአገሬ ውጣ እያልሽው አልተለፋደድሽም? አስታውሺ እያንዳንድሽ በደንብ ሰክረሽ ታውቂለሽ፣ ዐብይ ደርሶ በፍቅር አብዮቱ (Love Revolution) ድግሱ ቀዝቃዛ የሽሮ ፍትፍት ልባችን ላይ ጣል አድርጎ ከስካራችን እስኪያነቃን ድረስ እንኳን አንቺ ቅሪና ጳጳሳቱና ቀሳውስቱ፣አርቲስቶቹ፣ምሁራኑና የአገር ሽማግሌዎች እንኳን ሳንቀር ድብን ብለን ሰክረን ነበር፡፡ ሰካራሙ ሰውዬ እየለፈለፈና ወጪ ወራጁ እየሳቀ ሚኒባስ ታክሲው መገኛኛ ደርሶ ቆመ፡፡ ረዳቱ “መጨረሻው” ብሎ በሩን ከፍቶ ዱብ አለ፡፡
ሰካራሙ “ዋናው አድሮ መገኝቱ ነው የነገሰው ይበለን” በማለት የተለመደ ንግግሩን እየለፈለፈ ሁላችን ተከታትለን ወረድን፡፡ እኔ ከሰካራሙ ጎን ተቀምጣ የነበረችው ቸኳይዋን ቆንጆ ሴት ተከትዬ በመራመድ ወደ አዲሱ የመገኛኛ መናህሪያ ወይም ተርሚናል ለመሻገር የአስፋልቱ መክፈያ ላይ ካጠገቧ ቆምኩ፤ በዛው ቅጽበት ድልድዩ ስር መንገድ ላይ ዘርግተው የሚሸጡ ነጋዴዎች ድንገት የመጡባቸውን ደንብ አስከባሪ ፖሊሶች ለመሸሽ ሲፈረጥጡ መጥተው ቆንጆዋን ልጅ ከቆመችበት ገፈታትረው ከኋላ እየበረረ ለሚመጣ መኪና አቀበሏት፡፡
ስዞር የልጅቷ በድን አስፋልቱ ላይ ተዘርግቷል፡፡ ከጸጉሯ ስር ደም እንደምንጭ እየፈለቀ  ቁልቁል ይንደረደራል፡፡ ሰው ተሯሩጦ ከበባት “ምስኪን…እኔ ድፍት ብዬ ልቅር…የተረገመ መኪና ይህችን የመሰለች አበባም እንደዋዛ ከመንገድ አስቀራት” የሰዎች ድምጽና ለቅሶ እንዲሁም የልጅቷ የእጅ ስልክ ሲጠራ ይሰማኛል፡፡
በድን ሆኜ በቆምኩበት ሰካራሙ ሰውዬ ትከሻዬን በጁ ጨምድዶ ይዞ “ዋናው አድሮ መገኘቱ ነው፡፡ ዋናው የነገ ሰው መባሉ ነው፡፡” ሲለኝ ድምጹ በህልም አለም ውስጥ እንዳለ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ሳልፈልግ አፌን ከፍቼ መለሆሳስ ድምጽ አሜን አሜን አሜን አልኩ፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ከ “ተደምሬያለው!!” ባሻገር

ውኃ ይሰማል ጉድ በል አበሻ ውኃ ይሰማል አለች ፈረንጅ

ዶ/ር ዐብይ የህመም ማስታገሻ ወይስ መድሀኒት?