የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ


የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፡ መሪ ማለት መንገዱን የሚያውቅ፣በመንገዱ የሚራመድና መንገድ የሚያሳይ ነው፡፡”  
በመሪነት ዙሪያ በርካታ በሳል መጽሐፍትን ያስነበበን ታዋቂው አሜሪካዊ ፀሀፊና ተናጋሪ ጆን ማክስዌል እንዲህ የሚል አባባል አለው መሪ ማለት መንገዱን የሚያውቅ፣በመንገዱ የሚራመድና መንገድ የሚያሳይ ነው፡፡  እንደ ወረደ ሲነበብ “A Leader Is One, Who Knows The Way, Goes The Way and Shows The Way.” ይላል:: ይህ የማክስዌል አባባል መሪነት ራዕይና ተልዕኮ በመቅረፅ ብቻ የማያበቃና የተናገሩትን መሆንን የሚጠይቅ እንዲሁም ሌሎችን ማብቃትን የሚጨምር ከባድ ቀንበር መሆኑን ያሳያል፡፡ በተለይ መሪ ሆኖ አገር ማስተዳደር ከባድ ነው፤ ጥሩ የአገር መሪ መሆን መቻል ደግሞ የመሪነት ክብደቱንና ውስብስብነቱን በእጥፍ ይጨምረዋል፡፡ አንዳንድ መሪዎች እነርሱ የሚከተሉትን መንገድ ትክክለኛውና ፍጹሙ መንገድ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ ይሁንና አንድን አገር ለመምራት አንድ ትክክለኛና ፍጹሙ መንገድ የለም ወይም ገና አልተደረሰበትም፡፡ መሪነት ሂደት ነው፤ መሪነት ሙያ ነው፤ እናም ወደ ፍፁምነት ለመቅረብ የመሪዎችን የእድሜ ልክ የተማሪነት ፍቃድና መነሳሳት ይጠይቃል፡፡ ጆን ኤፍ ኬኔዲ እንዳሉት “መሪነትና ተማሪነት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው::” ጥሩ መሪዎች አገርን በእኩልነትና በፍታዊነት ስለማስተዳደርና በነጻነት ስለመምራት ከአቻዎቻቸው፣ ከታሪክና ከጊዜ ይማራሉ፡፡ ታላቅ መሪዎች ደግሞ ከጎረቤቶቻቸው ስህተት በተለይም ከገዛ ስተቶቻቸው ይማራሉ፡፡ብልህ መሪዎች ግን ከሁሉም ነገር ከእነሳሳት እንኳ ሳይቀር ይማራሉ፡፡
በአለፈው አስራምስት ቀን የሸገር ታይምስ እትም ብልህ መሪዎች ከእርሳስ ተፈጥሮ ሊማሩ ስለሚችሉት የመሪነት ጸጋ ፅፌ ነበር፡፡ እናም ይህ ወቅት መሪዎች ከኛ ህዝባችን ደግሞ ከመሬዎቹ ብዙ የሚጠብቅበት ወቅት ስለሆነ የበኩሌን ጠጠር ከመወርወር አንጻር ዛሬም መሪዎች ከዝይ ወይም በእንግሊዘኛው Geese ተብለው ከሚጠሩት ተሰዳጅ የወፍ ዝርያዎች መማር ስለሚገባቸው የመሪነት ክህሎቶች ጥቂት ለማለት ወደድኩ፡፡
ለአላማ ስኬት በጋራ መስራት
የዝይ ወፎች ሲበሩ የሚያሰሙትን ድምጽ ሰምቶ ወደሰማይ ቀና ብሎ ያስተዋለ ሰው ወፎቹ በ“V” ቅርጽ ሲበሩ ይመለከታል፡፡ አነዚህ ወፎች በ“V” ቅርጽ በመብረራቸው የተነሳ እያንዳንዱ ከፊት ያለ ወፍ በሚያደርገው እያንዳንዱ የክንፍ  እርግብግቦሽ ከሃላው ለሚከተለው ወፍ የመብረር ቅልጣፌና ቅለት እገዛ ያደርጋል ወይም የተከታዩ ወፍ በረራ“uplifted” እንዲሆን ያግዘዋል፡፡ እናም አንዱ ወፍ ብቻውን ከሚያደርገው የተናጠል ጉዞ ጋር ሲነጻጸር የ“V” ቅርጽ በመስራት ከሌሎች ወፎች ጋር በጋራ የሚደረገው በረራ በ71% የበለጠ ፍጥነት እንዲኖረው ይረዳዋል፡፡
በእኔ እይታ አገራችን መድረስ የምትፈልገው ቦታ መድረስ የምትችለው የኢትዮጵያን አንድነትና ብልጽግና የጋራ አላማ አድርገው በሚጋሩና ለአላማው ስኬት በጋራ በሚሰሩ መንግስት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የሀይማኖት ድርጅቶችና ህዝቦች ጥምረት ብቻ ነው፡፡ ልክ እንደ ዝይ ወፎቹ ሁሉ አንዱ ፓርቲ ሌላውን ፓርቲ፣ አንዱ ሀይማኖት ሌላውን ሀይማኖት፣ አንዱ ብሄር ሌላውን ብሄር ሳይንቅና ሳይጠራጠር አንዱ አንዱን በመደገፍና በመርዳት ላይ በተመሰረተ ወዳጅነት አንዱ  ለሌላው  ስኬት ክንፉን ማርገብገብ ከቻለ አገሪቷን በፍጥነትና በቀላሉ ወደምንፈልግበት ቦታ ማድረስ እንችላለን፡፡ በመተባበርና በመተማመን ብቻ የኢትዮጵያን ጉዞ ልክ እንደ ዝይ ወፎቹ  በ71% ማፍጠን ይቻለናል፡፡ 
በመስመር መጽናት
አንድ የዝይ ወፍ ለራሱ ያለው ግምት አኮፍሶት ወይም ማስተዋል እርቆት በሆነ አጋጣሚ ከአላማና ከሰልፉ ቢያፈነግጥና ብቻውን መብረር ቢጀምር ስህተቱን አርሞ ወደሰልፉ ለመመለስ ጊዜ አይፈጅበትም ምክንያቱ ደግሞ አብሮ በመብረር የሚያገኘውን ጥቅም ስለማያገኝና ብቻውን ሲበር የአየሩን ግፊት መቋቋም ስለሚሳነው ነው፡፡
አገር የሚመራ ፓርቲና መንግስት በተለያዩ አጋጣሚዎች የተነሳለትን አላማ ሊስትና ታሪካዊ ስህተቶችን ሊሰራ ይችላል በዚህ ወቅት “nothing worse than a proud leader” እንዲሉ በኩራትና በትቢት ተሸብቦ አለው አለው ብቻ ማለት አይኖርበትም፡፡ የሚማር ፓርቲና መንግስት ስህተት ሲሰራ ከመስመር ጋዶቹ በተለይም ከህዝቡ በግልጽ እገዛን መጠየቅ የሚደፍር መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ሁኔታ መንግስትና ገዢው ፓርቲ ልክ እንደ ወፎቹ ሁሉ የሌሎችን እገዛ በመጠቀምና ሌሎችንም በማገዝ የሚመራውን አገር በፍጥነት ማራመድና ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንዲችል ይረዳዋል፡፡ ከስህተት መመለስና እገዛ መጠየቅ ግን አያቴ እንደሚያደርገው ጋቢ መገልበጥ መሆን የለበትም፡፡ ለቅሶና ሽምግልና በመጣ ቁጥር ባልተለበሰው በኩል እየገለበጡ የውስጡን ቁሻሻ ለመደበቅ መሞከር አንድም ከክርፋት አያድንም ወይም ይህ አይነቱ ስንፍና እጥፋቱ እስኪያልቅ ድረስ ብቻ ነው ሊያዋጣ የሚችለው፡፡ እንደ ህዝብ የኛ ድርሻ መሆን ያለበት አገራችን ወደፊት መራመድ ትችል ዘንድ የአንድነት መስመራችንን ጠብቀን አንዱ ለአንዱ ስኬት ሰላማዊ ክንፉን በማርገብገብ የተልዕኳችን ዳር ላይ እንድንደርስ በመከባበር መተጋገዝ መቻል ነው፡፡
ተከታይ መሆን መቻል፡-
በመሪነት ሲያገለግል የቆየ የዝይ ወፍ ሲደክመው ያለማንም ግፊትና አስገዳጅነት በፍላጎቱና በሙሉ ፍቃደኝነት ለሌላኛው ወፍ ቦታውን በመልቀቅ ከኋላ ይሰለፍና እንደ አንድ የቡድን አባል የጋራ የሆነውን ጉዞ ማገዝ ይጀምራል፡፡
ታላቅ መሪ ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችል ተከታይ መሆን መቻል ይኖርበታል፡፡  እውነተኛ መሪ በሌሎች ችሎታና ብቃት ያምናል እናም ሁሌም እርሱ ብቻ መሪ ሆኖ ለመቆት አይታገልም፡፡ ቦታውን ለሌሎች በመልቀቅና ለሌሎች እድል በመስጠት ሌሎች ወደፊት እንዲመጡና እንዲመሩ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ለታላቅ መሪ ስልጣን የመጨረሻ ግብ ሳይሆን ህዝብና አገርን ማገልገያ በመሆኑ ሁለንተናዊ ውጤት ይመዘገብ ዘንድ በተለይ በአስቸጋሪ ጊዜ የተሸለ ሊሰራ ለሚችለው እድሉን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ይሰጣል፡፡ እውነተኛ መሪ እውነተኛ ተከታይ መሆን አይከብደውም፡፡ አገራችን ኢትዮጵያን  ሁሌም በሁሉም ሁኔታ ለመምራት ችሎታና ፍቃድ ያለው አንድም አካል እንደሌለ አምናለሁ፡፡ የአገራችን እድገት የተመሰረተውና የሚሳካው በሁሉም ብሄሮች፣ሀይማኖቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ፍቃድና መተባባር ላይ ነው፡፡
ሁልጊዜም ማበረታታት፡
የዝይ ወፎች በበረራ ወቅት የሚያሰሙት “ኳክ..ኳክ የሚል ድምጽ አለ፡፡ እያንዳንዱ ወፍ ያለማቋረጥ “ኳክ..ኳክ”በማለት ከፊቱ የሚበረውን ወፍ ፍጥነቱን እንዳይቀንስ በጩኸቱ ያበረታታዋል፡፡
የመሪ ጩኸት ህዝብን ለአንድነት ለስኬት የሚያነቋቋ መሆን ይኖርበታል፡፡ እውነተኛ  መሪ ህዝብን ለመከፋፈልና አገር ለመበተን አይጮህም፡፡ እውነተኛ መሪ ህዝብን በባዶ ቃላት ለመደለልና ለማታለል አይሞክርም፡፡ አገርና ህዝብ ወዳድ መሪዎች የሰርክ ስብከታቸውና ንግግራችው እውነተኛ አንድነትና ሰላም ነው፡፡ በዚህ ወቅት መንግስት ለህዝብ ሲጮህ፣ ህዝብ ለመንግስት ሲጮህ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ለህዝብና ለመንግስት ሲጮሁ፣ መንግስት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲጮህ አቅጣጫ የሚጠቁም፣የሚያነቃና የሚያስተሳስር ጩሀት መሆን ይኖርበታል፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት  ከሚዲያዎቻችን የምንጠብቀው የሰላም፣ የመግባባትና የአንድነት ጩኸትን ነው፡፡
በአስቸጋሪ ወቅት ድጋፍ መስጠት፡
አንድ ዝይ ወፍ በጉዞ ወቅት ቢታመም ወይም ቢጎዳና ከቡድን አጋሮቹ እኩል መብረር ቢያቅተው ሌሎቹ ወፎች በፍጹም ትተውት አይሄዱም፡፡ ይልቅስ ሁለት ወፎች ይመደቡለትና ያሳርፉታል፤ ከዛም ድኖ መብር እስኪጀምር ወይ እስኪሞት አብረውት ይሆናሉ፡፡
አገር ወዳድ መሪ የህዝቦችን የእርስ በርስ ትስስር እና የጋራ ታሪክ በማጉላት በችግር ወቅት የሚደጋገፉና የማይበታተኑ ጠንካራ ህዝቦች መመስረት ይጠበቅበታል፡፡ ዲሞክራሲያዊ መሪ ህዝቡን የሚያከብር፣ ለህዝብ ጥቅምና ፍላጎት የሚሰራ እንዲሁም በማንኛውም ሰዓት ወደ ህዝቡ በመውረድ የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄ መረዳትና መመለስ የሚችል መሆን ይገባዋል፡፡  እኔ እስከሚገባኝ ጠንካራ ግንባር የመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በችግር ጊዜ እጅ አይጠቋቆሙም፤ በፈተናም ወቅት ፈጽሞ አይበታተኑም ይልቅስ እንደ ዝይ ወፎቹ የታመመ ወይም የተጎዳ ጓዳቸውን እስከመጨረሻው በመንከባከብ የመስመር ታማኝነታቸውን ያሳያሉ እንጂ፡፡
ጎበዝ አገር መምራት ቀላል አይደለም፡፡ ታላቅና በህዝቡ የሚከበር መሪ መሆን እድል አይደለም፡፡ ነገር ግን እንደ ብልህ መሪ ሁልጊዜም ከሁሉም ነገር ለመማር ፍቃደኝነቱ ካለና ዙሪያችንን ለመመልከት ሶስተኛው አይናችን ከበራ ታላቅ መሪ የሚደርጉን ትምህርቶች በየቦታው አሉ፡፡ መሪ ማለት መንገዱን የሚያውቅ፣በመንገዱ የሚራመድና መንገድ የሚያሳይ ነው፡፡
ለምትሰማ ላንተ ኢዮብ እንዲህ ይልሀል “እስቲ . . . በሰማያት የሚበርሩ ወፎችን ጠይቅ ይነግሩህማል፡፡ የእግዚሀብሄር  እጅ ይህን እንዳደረገ፣ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?”፡፡ ቸር ወሬ ያሰማን!!!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ከ “ተደምሬያለው!!” ባሻገር

ውኃ ይሰማል ጉድ በል አበሻ ውኃ ይሰማል አለች ፈረንጅ

ዶ/ር ዐብይ የህመም ማስታገሻ ወይስ መድሀኒት?