ይድረስ ለሰኔ ጾም ረመዳንም እንዲሁ ልብ ይበል
ይድረስ ለሰኔ ጾም ረመዳንም እንዲሁ ልብ ይበል
፩
ጎጆዋ በብርዳማው ሌሊት ከግዙፉ ተራራ ቁልቁል ለሚንደረደረው የቅዝቃዜ ንፋስ እጅ ሳትሰጥ አባወራዋ
ልብ ውስጥ በሚንቀለቀለው የበቀል ትንታግ ነዳ ትጨሳለች፡፡
ዳገት እንደሚወጣ ሰው ሁሉ ቁጭ ባለበት ቁና ቁና ይተነፍሳል፣ ይቆምና እንደ ቆሰለ አንበሳ
ከመዲያ ወዲያ እየተንጎማለለ ያጉተመትማል፣አንጀቱን ይቆርጥለት ይመስል
የወገቡን መቀነት አስሬ ይታጠቀዋል፤ ፍልሚያ እንደጠማው አርበኛ ጠበንጃውን አሁንም አሁንም ይወለውላል፣ ጥይቱን አንድ ባንድ ወደ
ቡዋቡዋው ያጎርስና እንደገና አፈናጥሮ ያወጣዋል፤ ልክ ግዳዩን እንዳየ ነብር እጎጆው ግድግዳ ላይ የተንጠለጠለ የዱር ቅል ላይ ያፈጥና
አነጣጥሮ ባዶ ቃታ ይስባል፤ ጠበንጃውን አንድ ጊዜ በትከሻው ተሸክሞት ይቆማል ሌላ ጊዜ ደግሞ ጉልበቱ ላይ አጋድሞ እግሩን እያንዘፈዘፈ
ይቀመጣል፡፡ ከ27 ዓመታት በፊት ቤተሰቡ የተቃባውን ደም መልሶ ደም መላሽነቱን ለማረጋገጥ የቀረው የንጋት መምጣት ብቻ ነው፡፡
***
እንቅልፍ ላፍታም በአይኑ ሳይኳል ንጋት ዳልቻ የጉም ጋቢዋን ደርባ ውርጫም ፊቷን ገለጠች፡፡
በንዴት አንደጦፈ የጎጆውን በር ከፍቶ ምራቁን የደጅ መጋኛ ላይ ሲያርከፈክፍ…ምሽቱን በሙሉ አንዳች ሳትተነፍስ አንደ ክረምት ውሻ
ጥግ ላይ ተጠቅላ በፍርሀት ስትንቀጠቀጥ ያደረችው ሚሽቱ የሞት ሞቷን አፏን ከፍታ “ባዶ ሆድ ደግም አይደል፣ እስቲ ደረቅ ቂጣ እንካ
አፍህ ላይ አርገህ ውጣ” ስትል ተሰማች፡፡
ፊኛን አላልቶ ሽንት በቁም በሚያሸና
የቁጣ አይን ሚሽቱን ዞሮ እየገላመጣት “ዋ! ምን ትላለች ይቺ ሴት፣
ብዬ ብዬ ጦሜን ልግደፍ? የሰኔ ጦም መሆኑን ዘንግተሸው ነው ወይስ ጋኔል ተጣብቶሽ? በስመአብ በይ አንቺ” ብሎ በሩን ፊቷ ላይ
ደርግሞት ግዳዩን ጥሎ ደም ሊመልስ በቀል እያገሳ ተፈተለከ፡፡
፪
ሁለት ጾመኞች ናቸው፣ የጾም በየአይነት
አዘው ይመገባሉ፡፡
ጾመኞቹ የምግብ ቤቱ አስተናጋጅ በአጠገባቸው
አልፎ ከጎናቸው ያለ ጠረቤዛ ላይ ለተቀመጠ አንድ ተስተናጋጅ ሰው የአሳ ጥብስ ሲያቀርብ ተመልክተው አፍንጫቸውን በጣቶቻቸው እንደቆለፉ
በፍጥነት ቦታ ቀይረው ተቀመጡ፡፡በንዴት እንደጦፉ፡-
አንደኛው ጾመኛ፡- ‘’በቃ ኢቺ አገር
ሆዳቸው አምላካቸው በሆኑ ሰዎች ተሞላች?፡፡ አሁን እስቲ በጾም አሳ ባይበላ ይሞታል?’’ ብሎ ከንፈሩን መጠጠ::
ሁለተኛው ጾመኛ፡- አንገቱን እየወዘወዘና
አሳ ያዘዘው ሰው ላይ ክፉኛ እያፈጠጠ “ተመልከተው፣ ደሞ እኮ ልክ እንደ እውነተኛ ክርስቲያን የጌታችንን መስቀል አንገቱ ላይ አንጠልጥሏል፤አያናድድም?
ይነቀው፡፡” ሲል ተራገመ፤ ልቡ በአምላኩ ቅናት እየተቃጠለ፡፡
***
በዚህ መሀል አንድ ጨርቁ በገላው
ላይ ያለቀና ከግር እስከራሱ አቧራ የለበሰ ከሲታ ወፍ ከልክክል የጎዳና ልጅ ካስከተለው ጥቁር ውሻ ጋር የምግብ ቤቱን በራፍ ተደግፎ
እንደ ጉርሻ በጠቀለለው የቀኝ እጁ መዳፍ አመዳም ከንፈሩን ደጋግሞ እየነካ፣ በግራ እጁ መዳፍ ከወገቡ ጋር የተጣበቀ ሆዱን እያሸና
ድፍርስ አይኖቹን እያስለመለመ በምልክት የሚቀመስ ይለምናል፡፡
***
አንደኛው ጾመኛ፡- አስተናጋጁን በጩኸት
ጠርቶ “ምንድን ነው እንብላበታ፣ አባርልን እንጂ” ብሎ ሲቆጣ፤ አስተናጋጁ ረሀብተኛውን ልጅ ይገፈታትረው ጀመር፡፡
በጾም አሳ አዞ የሚበላው ሀጢያተኛው
ሰው አስተናጋጁን “እባክህ ልጁን ተወው” ብሎ ከገሰጸው በኋላ የሚበላውን አሳና ዳቦ ይዞ መጥቶ የልጁ አዳፋ እራፊ ላይ ገለበጠው፡፡
ሁለተኛው ጾመኛ፡-“ተመልከት፣ተመልከት
ይኼ አህዛብ የሚሰራውን ስራ፤ የራሱ መግደፍ ሳያንሰው ምንም የማያቀውን ህጻን አሳ መጽውቶ ሲያስኮንነው፡፡” እያለ እጁን በእልህ
ሲያወራጭ ጠረቤዛ ላይ የተቀመጠውን ጆግ ሙሉ ውሀ በአይበልባው አጩሎት ኖሮ
ጠረቤዛው ላይ ተከለበሰ፡፡
አንደኛው ጾመኛ፡- ከጠረቤዛው ላይ
ቁልቁል ወደ’ርሱ ከሚንደረደረው ውሃ ሳይበሰብስ ለማምለጥ ከተቀመጠበት ወንበር እመር ብሎ ሲነሳ ጠረቤዛውን በጉልበቱ ሽቅብ ነርቶት
ኖሮ የሚበሉት ምግብ ተሸቀንጥሮ ከወለል ላይ ተዘረገፈ፡፡
ሁለቱ ጾመኞቹ አይናቸው ምግባቸውን
ተከትሎ ከወለሉ እንደተዘረገፈ ልጁን ተከትሎ የቆመው ጥቀር ውሻ ኬት መጣ ሳይባል ተፈትልኮ ገብቶ መሬት የተደፋውን ምግብ ይነፈንፈው
ጀመር፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ