ከሽሮሜዳ እስከ መድሀኒአለም


ከሽሮሜዳ እስከ መድሀኒአለም
የእንጦጦ ዛፎች በተራራው ፍቅር ተጠምደው ከፈዘዙ የደመና ራሶች ጎፈሬ ላይ ጠል እያራገፉ ቁልቁል ከሚያርከፈክፉብን ካፊያ ስር ለታክሲ ወረፋ ከስፔን ኤንባሲ በር እስከ ታላቋ አሜሪካ ኤንባሲ አፍንጫ ድረስ በማለዳ ሽሮ ሜዳ ተሰልፈናል፡፡ እንደ ቀንድአውጣ ስንሳብ ቆይተን በቁፋሮ የተገኝ የሚመስል አቧራ የዋጠው ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ተራ ደርሶን ተጠቀጠቅን፡፡
ታክሲው ቁልቁለቱን ወደ ስድስት ኪሎ ሲንደረደር አሜሪካ ኤንባሲ ፊት ለፊት ለይለፍ ወረቀት የተሰለፈውን ሰው ስመለከት ከጦርነት በቀር የሰልፈኝነት እጣ ፈንታ የተጣፈለት ትውልድ መሀል መሰንቀሬን ክፉኛ በሀሳቤ አማርር ጀመር (ከጦርነት በቀር ስል ግን በኔ ትውልድ በትንሿ የድንበር ከተማ ባድመ የተካሄደውን “የሁለት መላጦች የማበጠሪያ ጦርነት” ዘንግቼው ሳይሆን ተዋግተን የቆሰልንበት፣ ገለን የሞትንበት፣ሞተን ያልተከበርንበት እና አሸንፈን ያልተሸለምንበት በመሆኑ ከጨዋ ጦርነት ስለምጥፈው እንጂ)፡፡ ስሪያ ላይ እንዳለ ቀበሮ የቀጠነ ድምጽ ያላት ሴት ድንገት “መድሀኒአለም ወራጅ አለ” ብላ ከምሬቴ አነጠፈችኝ፡፡ የታክሲው ወያላ እያለ እስቲ እኔ ምን አባነነኝ?
ለነገሩማ ታክሲ ላይ አይሁን እንጂ ሁላችንም ወያሎች ነን፡፡ ለፍርፋሪ ያደሩ ምንዱባን ድሆች ኩርማን ለሚጥሉላቸው ግብዝ ባለጸጎች ይወይላሉ፣የሙያ ክብር ያልገባቸው ጋዜጠኞችና የቆሙለትን አላማ የካዱ መገናኛ ብዙሀን የህዝብን ጩኸትና የአገር ታሪክ ችላ ብለው ለባለስልጣንና ለጊዜው ፖለቲካ ይወይላሉ፣ተልካሻ ደራሲና ጸሀፊ ሌሎቹም ጥበበኛ ነን ባዮች ጥበብን አዋርደው ለገንዘብና ለዝና ይወይላሉ (አሁን አሁን ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ተከትለው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያና ካፌ ከፍተው “ምን ልታዘዝ?” አዲስ ሲትኮም ምናምን የሚሉ ጥበብን “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” ያሰኙብን ዘፋኞች፣ ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶችና መገናኛ ብዙሀን በፊት የት ነበሩ? እየወየሉ አልነበሩምን?)፣ሆዳም ባለስልጣናት አገርና ህዝብን ክደው ለጥቅም ይወይላሉ፣አድርባይ ምሁራን አመክንዮና ፍልስፍናን ንቀው ለሆድ ይወይላሉ፣እውቀት የጎደለውና በዘመድ አዝማድ የተሳበ ጨዋ ሰራተኛ ለአለቆቹ ይወይላል፣ሀይማኖተኛ ነኝ ባዩ ሳይቀር ክርስቶስን ዳግም ሸጦና ነብዩ ሙሀመድን (ሰ.ዐ.ወ) አሳዶ ለስጋው ይወይላል፡፡ ማንንም ሳፈሩና በምንም ሳይደለሉ ለእውነትና ለሙያቸው ክብር ዘብ ቆመው ካየናቸው ጥቂቶች በቀር ደረጃውና ቦታው ይለያይ እንጂ ሁላችንም ወያሎች ነበርን ነንም፡፡
የሰልፍ ብዛት እና የሰኔ ዝናብ ካጋቡብኝ የሀሳብ ንጭንጭ ተመልሼ ቀጭኑ ድምጽ ወደ መጣመት አቅጣጫ አንገቴን ሳዞር ወራጅ ካለችው ሴት ጋር አይናችን ተላተመ፡፡ ቅድም ከፊቴ ተሰልፋ የነበረች ልጅ ናት እኔ ሀቀኛ የመንግስት አገልጋይ ያውም ጠመኔ ቀቢ መምህር በመሆኔ ካቦርትም ጥላም ስለሌለኝ ከካፊያውና ከብርዱ የተጠለልኩት በዚች ሴት ሀሳብ ነበር (አንድም በአጭር ቀሚሳ ያጋለጠችውን ባቷን እቤት ወስጄ እየሞኩ፣ ሁለትም ወራሪው ክረምት የባቷን ውበት በሱሪ እንዳይሸፍነው አከርካሪውን ሰብራ ለውበቷ የቆመች ጀግኒት በመሆኗ ከጣይቱ ተራራ ስር በቅላ ባትሆን ኖሮ ነበር የሚቆጨኝ እያልኩ ሜዱዛዊ የአርበኝነት ተጋድሎዋ አሙቆኝ)፡፡ ወያላው ልጅቷን ለማሶረድ የታክሲው በርላይ የተተበተበ ሲባጎ እየጎተተ በሩን ለመክፈት ሲታገል እሷ ለመውረድ ባጎነበሰችበት ሁለት ጡቶቿ ፊለፊቴ ተደቀኑ፤ የታክሲው ጣራ ማጠርና በሩ አልከፈት ማለት ከአምስተኛው ሰማይ እንደታዘዘልኝ በመቁጠር ምነው ወስዳ በጉዲፈቻ ባሳደገችኝ እያልኩ ባለሁበት ብሽቁ ወያላና የታክሲው በር ተባብረው ልጅቷን ምስካየ ህዙናን መድሀኒአለም ፊት ለፊት አስወረዷት፡፡
ልጅቷ በወረደችበት ቅጽበት አንድ ሰነፍ ተማሪ በሚጠላው የትምህርት ክፍለ ጊዜ በሚያቋርጥ እስክርቢቶ የሳላቸው የሚመስሉ ብጭርጭር ሽማግሌ የቆየ የአበሻነት የስራ ልምዳቸውን ተጠቅመው ልጅቷን ያሟት ጀመሩ (ዞር ካልክ የማያርድህ የለ መቼም):: “እስቲ መድሀኒአለም ያሳያችሁ” አሉ ሽማግሌው ሰው የሜዳ አድቫንቴጃቸውን ለመጠቀም ወደ ስደተኛው መድሀኒአለም ቤተክርስትያን ሹል ጣታቸውን እየጠቆሙ “ይቺ ሴት ወጣት ናት፣ ትኩስነቷን በመራቆቷ ብቻ ከምትገልጸው ምናለ ከሽሮሜዳ እስከ መድሀኒአለም ለመምጣት ከኛ ከደካሞቹ ጋር በዝናብና በብርድ ተሰልፋ ውድ ጊዜዋን ከምታባክን በግሯ ብትመጣ? ወጣትነቷ እንድ ቦታ ቆሞ በዝናብ መበስበስን እንዴት መረጠ? ወጣት ቆሞ ከሚረጥብ እየሄደ ቢበሰብስ አይሻለውም?” ሽማግሌው የማንንም መልስ ሳይጠብቁ ቁችትና ብርድ በሚያቀጠቅጠው ሾካካ ድምጽ “ምን ታድርግ ብላችሁ ነው? ሽሮሜዳ ተሳፍራ እስከ መድሀኒአለም መሄድና ወራጅ አለ ማለት እንዴትስ ከብዶ ያሳፍራት? አሷስ ብትሆን ከናቱ ጉያ ሳይወጣ በቤተሰቡ ጫንቃ ላይ እንደታዘለ የተገረዘበት አልጋላይ የሚገነዝ ብላሽ ትውልድ አካል አይደለችምን? የሩቅ ትልም የሌለው ባቋራች በተሞላ መንገድ የሚተራመስና የሚሰደድ የተረገመ ሽንት ፍሬ ባትሆን ነበር ከሽሮሜዳ ተሳፍራ መድሀኒአለም መውረድ የሚያሳፍራት” እያሉ ወጣቷን ማሳቀላቸውን ቀጥለዋል፡፡
ሽማግሌው “ከሽሮሜዳ እስከ መድሀኒአለም” እያሉ የትችታቸው አዝማች አርገው የደጋገሙት ሀረግ ህሊናዬ ላይ እየጮኸ ዳግም ሀሳብ ይዞኝ ጭልጥ አለና አስተውሎ ለተመለከተው ልክ እንደ ወጣቷ ሴት ጉዞ የአብዛኛው አበሻ የህይወት ጉዞም ከሽሮሜዳ እስከ መድሀኒአለም ድረስ ነው ስል አሰብኩ፡፡ አዎ ሽሮ በልቶ ለማደርና ለማሳደር በሽሮ ሀሳብ ናላው የናወዘበት አባወራ ከሽሮ ሀሳቡ ለማረፍ አረቄውን ተግቶ ይመጣና በሽሮ ሀሳብ ስትጦዝ ማጀት ከዋለች ሚስቱ ጋር ይተኛል፡፡ እኛ አበሾችም በሽሮ መንስኤነት እንጸነሳለን፣አበሻዋ እናታችን ሽሮ እየበላች ትወልደንና አድገን ሽሮ የምናመጣ እንሆን ዘንድ ደረቅ እንጀራ ላይ እየተንከባለልን እንመረቃለን፣ ከዛም ሽሮ እየበላን በሽሮ እናድጋለን፣ በሽሮ ለሽሮ እንማራለን፣ለሽሮ ተቀጥረን ለሽሮ እንሰራለን፣ለሽሮ እናምናለን ለሽሮ እንክዳለን፣ለሽሮ እንወዳለን ለሽሮ እንጠላለን፣ለሽሮ እንሰደዳለን ለሽሮ እንዋረዳለን፣ለሽሮ እንገላለን ለሽሮ እንሞታለን፣ለሽሮ እንፈራለን ለሽሮ እናፍራለን፣ለሽሮ ቤሳ ድርሰት እንጽፋለን ለሽሮ ዝምታን ፈርተን ጩኸት ጩኸቱን እንዘፍናለን፣ንጉስ ብንሆን እነኳ ለሽሮ ተሹመን ለሽሮ እንወርዳለን፡፡ መላ ማንነታችን ሽሮ በማሳደድ በሽሮሜዳ ፍልሚያ ተጠምዶ የመንፈስ ማንነታችን ከሽሮ የዘለለ ትርጉም ሳይኖረውና ከሆድ ባሻገር ያለው ብርሀናችን በገሀድ ሳይገለጥ የሆዳችን ባሪያ እንደሆን መድሀኒአለም ጋር ደርሰን ጥቂቶች ወራጅ አለ ብለን ብዙዎች ደግሞ ተገፍትረን ከመቃብር እንወርዳለን፡፡
በሽሮሜዳ ግርግርና ወከባ ተሰልበንና ውስጣዊ መረጋጋታችን ተነስቶ ከቶ ከራሳችን ጋር ሳንወያይና ወደ ውስጣችን ተመልክተን የተሰጠንን ልዩ የህይወት አላማ፣ተልኮና ተሰጥኦ አውቀን አንዲት ቀን እንኳን ሳንኖረው ትርጉም አልባ ሩጫ እንደሮጥን ትርጉም የለሽ እረፍት እናርፋለን፡፡ ከሽሮሜዳ ትግል ማግስት ሁላችን የሚቀረን መድሀኒአለም መውረድ ብቻ ይሆናል፡፡ ልክ እንደ በጎቹ ሁሉ ማለዳ ወደ ሳርና ውኃ ሰርክ ወደ ጉሮኖ በመመላለስ ብቻ ያለምንም ታሪክና ማስታወሻ መድሀኒአለም ደርሰን ከህይወት ታክሲ እንወርዳለን፡፡
ታክሲው ስድት ኪሎ ዩንቨርሲቲ በር ላይ ሲደርስ “ወራጅ አለ” ብዬ ወረድኩ፡፡ ሀሳቤን በህሊናዬ እንዳዘልኩ ቀጥታ ክፍል ገባው ተማሪዎች ቀድመው ክፍል ገብተው እየጠበቁኝ ነበር፡፡ ለደቂቃዎች ምንም ሳልተነፍስ ቆሜ ሳስተውላቸው ቆየውና ጥቁሩ ሰሌዳ ላይ እንዲህ ስል ጻፍኩ፡-
ከሽሮሜዳ እስከ መድሀኒአለም፡- በዚች አገር (ምድር) እኔና እናንተ ሽሮሜዳ ተሳፍሮ መድሀኒአለም ከመውረድ በላይ ተልኮና አላማ የለንምን?

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ከ “ተደምሬያለው!!” ባሻገር

ውኃ ይሰማል ጉድ በል አበሻ ውኃ ይሰማል አለች ፈረንጅ

ዶ/ር ዐብይ የህመም ማስታገሻ ወይስ መድሀኒት?