ሶስቱ ሱሰኛ ካድሬዎች


ሶስቱ ሱሰኛ ካድሬዎችና ሌላ፡- በሌላ ቦታና ጊዜ
በአረጀውና በአስቀያሚው “ርዕዮተ አለም” በርጫ ቤት ውስጥ ቅጠላቸው የተራቆተ የጫት እንጨቶች የተበተነ የደመራ ጭራሮ መስለው ተከምረዋል፤ የሞቱ ሲጃራዎች መተርኮሻ ውስጥ በግንባራቸው ተተክለው በአመድ ተቀብረዋል፤ ጭንቅላቱ ላይ የከሰል ፍም እንደ አክሊል የጫነ የሺሻ እቃ በገረባ ተከቦ እንደ ሃውልት ተገትሯል፡፡ ሶስቱ የአሮጌ ዘመን ካድሬዎች የምርቃናቸው ኒርቫና[1] ላይ ደርሰው በተመስጦ ያወራሉ፡፡
አንደኛው ካድሬ፡- በልማት ስራ ጭቃ የጎረሱ የጥፍር ጫፎች ባሉት አመዳም ጣቶቹ ለአብዮት የከረደደ ጸጉሩን እንደ ነጠላ እየቋጨ እንዲህ ሲል ተናገረ፡- “እኛ ለህዝቡ የመረጥነው መንገድ ውሃ አይገቤ[2] መንገድ ነበር፡፡ የድሮ ታሪክ (በተለይ መልካም መልካሙ)፣ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ አርበኝናትና ፋኖነት የሚባሉ የድሮ ስርአቶችና የስርአቱ ናፋቂዎችን ጎርፍ በጥላቻ ሃውልትና በግምገማ ገትሮ ማቆም የሚያስችል water proof መንገድ፡፡ ምን ያደርጋል “የአህያ ስጋ መሬት አልጋ ሲሉት መሬት አለ” ያ ዲክታተር መንግስቱ እውነቱን ነው፡፡ እኛ ግን በዚችን አገር የፖለቲካ፣ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የፍልስፍናና የታሪክ ባዘቶ ውስጥ ቀላቅለው ሊፈትሉን የማንቻል ተራራ አንቀጥቃጭ ነጻ ትውልዶች መሆናችንን ልማታዊ ደራሲና ጋዜጠኛ በታሪክ ይመሰክራል፡፡”
******
ሁለተኛው ካድሬ፡- ከሌባ ጣጡና ከመሀል ጣጡ ስር ተሸብልቃ ካለች የአዲስ ራዕይ ትንባሆ ጡት የላገውን ጢስ በአፍንጫው እያሶጣ እንዲህ አለ፡- “ህዝቡ ተደስቶ እንዳይኖር የራሱ ጠላት እራሱ ህዝቡ ነው፡፡ ከታላቁ መሪያችን በላይ ያለ አድማጭ ተናጋሪ፣ያለ ተከታይ መሪ፣ያለ ነገ ባለራዕይ እንዲሁም እንደ ሶምሶም በቁም ካሰለፋቸው በሞቱ ያንጋጋቸው እልፍ የሆኑለት ሌላ መሪ በዚች አገር ያለና ይገኝ ይመስል ህዝብ ይለፋል፡፡ ፍቅር የሚባል አብዮት ለክርስቶስም አልበጀው ያተረፈለት መገረፍና መሰቀል ብቻ ነው፡፡ ቆይ ግን ህዝባችን ከጠንካራ መደበቂያው ከኤሊ ድንጋይ ይልቅ ስስና ረጋፊ የርግብ ክንፍ የሚመርጠው ለምድን ነው?”
******
ሶስተኛዋ ካድሬ፡- በቀጭኑ የቱቦ አንጀት አማካኝነት በትንፋሿ ተኮርኩሮ ከሚንተከተከው የሺሻ ሆድ ዕቃ ሳንባ ሙሉ (የስብሰባና የግምገማ ወሬ) ጢስ ስባ እያንበለበለችው በሻከረ የሴቶች ሊግ መሪ ድምጽ ተናገረች፡- “ሴት ልጅ ምን ሲነካት በፍቅር ስም የአንድ ወንድ የደረት ጌጥ ለመሆን ትመርጣለች? ምንስ ልቧን ሲሰውራት በትዳር ስም እስረኛ ለመሆን ጣቷን ለባል ትሰጣለች? ማንስ አቅሏን ሲያስታት በእናትነት ስም የልጅ ሞግዚት ለመሆን ትሞኛለች? ስለምንስ ሴትነቷን ያህል ዲግሪ ታጋይነቷን (ዘሯን) ያህል ታላቅነት ይዛ በትምርትና በስራ ትባክናለች?”፡፡ ይህ ነው የሴቶች እኩልነትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጫው፤እንጂማ ሴትን በአደባባይና በየሸንጎው ማመስገን ማይ ያቅተዋል (ታላቁ መሪያችንም ሆነ አቶ ኃይለማሪም ይህ ጠፍቷቸው አልነበረም)፡፡
******
ሱሰኞቹ ካድሬዎች አሮጌዋ ርዕዮተ አለም በርጫ ቤት እንደፈረሹ በምርቃናና ድንዛዜ እንዲህና እንዲያ ሲሉ..ሲሉ..ሲሉ..(፣ሲሰበሰቡና ሲሰበስቡን፣ ሲገማገሙና ሲገመግሙን፣ሲታደሱና ሲቆሽሹ (ማጠብ እደሰነፈች ባልቴት ጋቢ ሲገለብጡ) መሽባቸው፡፡ ሲመሽ እንኳ (የሶስት አስርተ- ዓመት) ምርቃናቸው በቀላል አልሰበር ማለት ለጨብሲ ደግሞ አሶጣቸው፡፡ በጨብሲ ዘመን ጠጥተው በአስቸኳይ አዋጅ ሌሊት ሳይቀር ደንሰውና ተዳርተው ሲያበቁ (በሰው ጩኸት) ምርቃናቸው ተሰብሮ ሳለ ለስካራቸው ንጋት መጣች፡፡ (የተማሩ ከአዲሷ ንጋት ጋር ሲገጥሙ) ሶስቱም ካድሬዎች ግን በፍርሀት እያለከለኩ ከንጋት ሽሽት ሮጠው ከአንዲት አሮጌ ጫት ቤት ፊት ለፊት ቆሙ፡፡
አንደኛው ካድሬ የጫት ቤቷን መስኮት በሃይል እየደበደበ “ባለጫት እባክህ ክፈትና ያደረ ጫትም ቢሆን ስጠን! የዐብይ ዘመን ንጋት እያሳደደን ነው፡፡ ብሎ ጮኸ፡፡”
ሌላ በሌላ ቦታና ጊዜ፡-
አንዱ ጥንብዝ ብሎ ሰክሮ እየተወዛወዘ ሽንቱን ይሸናል፡፡ ሽንቱ አስፋልቱ ላይ መስመር እየሰራ ቁልቁል ተንድርድሮ በማስቲሽ ሰክረው እንደውሻ ተጣጥፈው የተኙ አመዳም የጎዳና ልጆች የመኝታ ካርቶን ስር ይገባል፡፡ ሰካራሙ እተኮለታተፈና ምራቁን እየረጨ “ህዝብ ማለት መንግስት ነው” ሲል ሰማሁት፡፡
የትራፊክ መብራት አቁሟቸው የሚለመኑ ባለመኪኖች፣በወሲብ ንግድ በተሰማሩ ጨቅላ ህጻናት ጭን ገንዘብ ከፍለው የሚደሰቱ ሴሰኞች፣ የቤት ሰራተኛቸውን የስራ ባሪያ ያደረጉ እመቤቶች(የወሲብ ባሪያ ያደረጉ አባወራዎችም)፣ ሹፌር ትራፊክ እዛጋር አለልህ የሚሉ ተሳፋሪዎች፣ ምንዱባንና ደሃ ከቤተክርስቲያን እየደበደቡ የሚያባርሩ ጸሀፍት ፈሪሳውያን እንኳን ሳይቀር “ህዝብ ማለት መንግስት ነው” ሲል ሰማኋቸው፡፡
እንደገናም ሌላ፡-
የመንደራችን ሰዎች ለደገደገች፣ ጧሪና ቀባሪ ላጣች ደራቁቻ ባልቴት ሴት ቤቷ በላዪ ላይ ፈርሶ ሳይገላት ብለው አዋተው ያደሱትን የቀበሌ ቤት የወረዳችን አመራር የእድሳት ፍቃድ የለውም ብሎ ቆሞ አስፈርሶ ቆርቆሮውን አሸክሞ እያሶሰደ “መንግስት ማለት ህዝብ ነው” ሲል ሰማሁት፡፡
የወረዳችን የደንብ አስከባሪ ፖሊስ የአክስቴስ ቦርሳ መንትፎ በአጠገቡ የሚሮጠውን ሌባ “የኔ ስራ ወንጀለኛ መያዝን አይደለም ይኼ የፖሊስ ስራ ነው” በማለት አስመልጦት መንገድ ላይ የሚነግዱ ወጣቶችን በቆመጥ እየዠለጠ እያባረረ “መንግስት ማለት ህዝብ ነው” ሲል ሰማሁት፡፡
ሁለቱም ያሉትን ሰማሁ እንጂ ትረጉሙ ግን ፈጽሞ አልገባኝም፡፡



[1] ኒርቫና (Nirvana) በቡዲዝም እምነት የመጨረሻው የብቃት/የንቃት ደረጃ ሲሆን የምርቃናን የመጨረሻ ደረጃን ለመግለጽ ተጠቀምኩበት
[2] ውሃ አይገቤ፡ water proof የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል ለመተካት የተጠቀምኩበት የራሴ ቃል

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ከ “ተደምሬያለው!!” ባሻገር

ውኃ ይሰማል ጉድ በል አበሻ ውኃ ይሰማል አለች ፈረንጅ

ዶ/ር ዐብይ የህመም ማስታገሻ ወይስ መድሀኒት?