መሀረቤን ያያችሁ?
መሀረቤን
ያያችሁ?
ዛሬ፡-
እመት የቢጫወርቅ ከፊሉ ሳር ከፊሉ ቆርቆሮ በለበሰ ጣራ ስር፣በከፊል
ከሲሚንቶና ከብሎኬት በከፊል በጭቃ ተዋቅሮ በግማሽ ቢጫ በግማሽ ጥቁር የተቀባ ግድግ ካቆመው ጎጆ አይሉት ቪላ ቤት ውስጥ፤ በግማሽ
ከጠፈር በግማሽ ከሽቦ ተሰርቶ ግማሽ የሳር ግማሽ የስፖንጅ የሆነ ፍራሽ ከተካደመበት አልጋ ላይ፣ የፊታቸው ገጽታ በከፊል ፈግጎ
በከፊል እንደጠለሸ፣ በቀኝ አይናቸው የተስፋ ብርሃን እየረጩና የግራ አይናቸው በበኩሉ በፍርሀት እንደተሞላ፣ ከፊል ሰውነታቸው ጤና
ሆኖ ከፊሉ በደዌ እንደተመታ በመንቃትና በእንቅልፍ መሀል ሆነው በተንጋለሉበት በታከተው ሰው ድምጽ ደጋግመው ልጆቻቸውን ይማጸናሉ፡፡
ልጃቸው የእናቱ ልጅ ቆራሌ ወንድሞቹ በየመንደሩ “አሮጌ ቆርቆሮ
ያለው” እያሉ ዞረው እየሰበሰቡ እቤት በሚከምሩት ቅራቅንቦ የተነሳ ያደፈውን የእናቱን መጎናጸፊያ ከብዙ ትርኪሚርኪዎች መሀከል ለመለየት
ብቻውን ይታገላል፡፡ ልክ ሊያገኘው ሲል ልዋጭ ወንድሞቹ በበኩላቸው የእናታቸው የጥንት ግን ዝንተ-ዓለም አዲስ የሆነ መጎናጸፊያ
አረጀ ብለው የነሱን አሮጌ አዲስ አስመስለው “ልማጭ ልዋጭ” እያሉ አዲሱን መጎናጸፊያቸውን በአሮጌ መሀረብ እየለወጡ አምጥተው ከቤት
ያጠራቀመት የመሀረቦች ዲሪቶ ይናድና ሊገኝ ያለውን የእናቱን መጎናጸፊያ ይቀብርበታል፡፡ የእናቱ ልጅ ሳይታክት በብዙ ትግል ከብዙ
ቅራቅንቦዎችና ዲሪቶዎች መሀል የእናቱን መጎናጸፊያ ዳግም ያገኘው ሲመስለውና በቀኝ እጁ ከፍ አርጎ ይዞ ለእናቱና ለወንድሞቹ ሊያሳያቸው
ሲጣጣር ሌላ ያልታሰበ የመሀረቦች ቅራቅንቦና ዲሪቱ እንደገና ከየስርቻው እንደ አሸን እየፈሉ ተከምረው ይናዱበትና የእናቱን መጎናጸፊያ፣
እናትና ወንድሞቹን ይከልሉታል፡፡
የእናቱ ልጅ ተስፋ ሳይቆርጥ እንደምንም ተፍጨርጭሮ ከማህረብ ክምር
ማህል የእናቱን መጎናጸፊያ ፈልጎ አውጥቶ ከፍ ሊያደርገው ሲል ድቅድቅ ጨለማ ከወረሰው ከጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ በአረጁና በገረጀፉ ዛፎች
ቅርንጫፍ ላይ እንደ ቅጠል የበቀሉ ልዩ ልዩ ቀለም ያላችው አዳፋ ማህረቦች በአውሎ ንፋስ ተገፍተው እየረገፉ እሱና የእናቱን መጎናጸፊያ
ሊቀብሯቸው ሲታገሉ ጮሆ ከእንቅልፉ በመባነን “የእናቴን መጎናጸፊያ” እያለ ከቅዬው አደባባይ ወጣ፡፡
የዛሬን
አያርገውና፡-
በእመት የቢጫወርቅ ልጆች ደካማነት የተነሳ ታሪካቸው ተረት፣ በልጅ
ልጆቻቸው መፍዘዝ የተነሳ ደግሞ ሚስጢራቸው ጊዜ ማሳለፊያ እንቆቅልሽ ሳይመስል በፊት እመት የቢጫወርቅ ባለብዙ ታሪክና የታላላቅ
ሚስጢራት ባለቤት ነበሩ፡፡
እንደዛሬ ልጆቻቸው በስደት ሀሞታቸውን ሳያፈሱና የልጅ ልጆቻቸው
በእንቶፍንቶ ክርክር መቅኗቸውን ሳያንጠፈጥፉ በፊት እመት የቢጫወርቅ ማህጸናቸው የተባረከላቸው የብዙ ሴትና ወንድ ጀግና ልጆች እናት
ነበሩ፡፡ ልጆቻቸው ለእናታቸው ክብርና ለነጻነታቸው ሞትን የናቁ የወንድ ወንዶች ነበሩ፡፡
እንደዛሬ ስንፍናና ሱስ እግር ከወርች ሳይቆልፋቸው በፊት የእመት
ቢጫወርቅ ልጆች ልመና የሚያስነውራቸው መሬት ሲያርሱ፣ከብት ሲያግዱ፣እንጨት ሲፈልጡና ወፍጮ ሲፈጩ የሚውሉ ታታሪ ሰራተኞች ነበሩ፡፡
እንደ ዛሬ ድንቁርናቸውን በጥቁር ካባ በመከለል መጠምጠምን ከማወቅ ሳያስቀድሙ በፊት የእመት የቢጫወርቅ ልጆች ጥበብን አጥብቀው
የሻቱ የስነ ከዋክብት፣ የስነ ህንፃ፣ የእደ ጥበብና ተግባረ እድ፣ የስዕል፣ የሙዚቃ በአጠቃላይ የሳይንስን የፍልስፍና ቀደምት ሊቀ
ሊቃውንቶች ነበሩ፡፡
እንደዛሬ ቅዬው በረብየለሽ ሁካታና ግርግር ሳይሞላ በፊት የቅዬው
ነዋሪዎች እድርና እቁባቸውን በትነው ጂጌ፣ወንፈልና ማህበር ለምኔ ብለው ብቻ ለብቻ መውረግረግ ሳይጀምሩ በፊት፤ሰፊዋን መንደር ሸንሽነው
በኮሽም እሾህ እያጠሩ የየራስ ክልል አበጅተው አንሰው እናታቸውን ሳያሳንሱ በፊት፤በጎጇቸው ሳይቀር ታላቁን አይጠየፍ መሰብሰቢያ
እልፍኛቸውን እልፍኝ፣ መኝታቤት፣ መአድቤት ብለው አስምረው ተከፋፍለው ከመኳረፋቸውና በራቸውን ዘግተው ጎሬቤት ጠል ከመሆናቸው በፊት፤እንደ
ዛሬ የእናታቸውን መጎናጸፊያ እንደ ክርስቶስ ቀሚስ ተቀራምተው ትናንሽ መሀረብ ሳያደርጉት በፊት እመት የቢጫወርቅ የሰላምና የአንድነት
እናት ነበሩ፡፡ የቅዬው ነዋሪዎች በሙሉ፣ አእዋፍና አራዊት ተራራና ወንዞች እንካን ሳይቀሩ በእመት የቢጫወርቅ ቀሚስ ስር ተጠልለው
በፍቅርና በትብብር የሚኖሩባቸው ታላቅ ዋርካ እመቤት ነበሩ፡፡
እንደዛሬ ልጆቻቸው ከስጋ፣ ከነፍስና ከመንፈስ መሰራታቸውን ዘንግተው
ስጋቸው ከአካባቢያቸውና ከሆዳቸው ምግብ ጋር እየተሻረከ ባላበሳቸው ቆዳ ተበልጠውና ምላሳቸው ከተወለዱበትና ከኖሩበት አካባቢ ኮርጆ
በሚለፈልፈው ልሳን ተቂለው መንፈሳዊ ማንነታቸውን ሳይዘነጉና ቅጥባጣ የማንነት ጥያቄ አዘቅት ውስጥ ሳይወድቁ በፊት የእመት ቢጫወርቅ
ልጆች ያለድለላና ውስለታ የሚከባበሩ ታላቅ ቤተሰብ ነበሩ፡፡
ዛሬ፡-
ዛሬ የእመት የቢጫወርቅ ልጆች መንገድ ጠፍቷቸውና ግራ ገብቷቸው
እሜቲቱን ስመው ሳይጨርሱ እየነከሷቸው፣ አቅፈው ሳያበቁ እየገፈተሩዋቸውና አንድ ብስል አንድ ጥሬ እያጎረሷቸው የልጆቻቸው ግራ መጋባት
ግራ አጋብቷቸው የልጆቻቸው መውረድና ማነስ አውርዶ አሳንሷቸው፤ ስቀው እንደተከፉ፣ ተስፋ አርገው ቀቢፀ ተስፋ እንዳጠላባቸው በመንታ
እግር በመንታ የእጣ ፈንታ መንገድ ላይ በግማሽ ቆመው በግማሽ ወድቀው በጎጆ አይሉት ቪላቸው ውስጥ ይቃትታሉ፡፡ ከሁሉ በላይ አሮጊቷን
እመቤት ጤና የነሳቸውና ታማኙ ልጃቸው የሆነውን የእናቱን ልጅ መረጋጋቱን የነጠቀው እናቱ ሁሌም ከትከሻቸው የማይነጥሉት የመጎናጸፊያቸው
መጥፋት ነው፡፡
የዛሬን
አያርገውና፡-
ልጆቻቸው የእናታቸውን መጎናጸፊያ እየደረቡና መጎናጸፊያው ብርታትና
ግርማ እየሆናቸው ስንቱን ዳገት ወጥተው ስንት ቁልቁለት ወርደዋል፤ ስንቱን ሸንተረር አቋርጠው ስንት ወንዝ ተሻግረዋል፡፡ ሲደክሙ
በመጎናጸፊያው ላባቸውን አብሰውበታል፣ ሲደሙና ሲቆስሉ በመጎናጸፊያው ደማቸውን ጠርገው ቁስላቸውን አስረውበታል፣ መጎናጸፊያው ሲፈሩ
የመሸሸጊያ ድንኳናቸው ጌጥ፣ ሲያለቅሱ የእንባቸው ማበሻ እየሆነ ተጽናንተውበታል፡፡
ልጆቻቸው በመጎናጸፊያው ሀይል ለመጎናጸፊያው ክብር እሮጠው አሸንፈዋል፣
ታግለው ጥለዋል፣ ተፋልመው ድል ነስተዋል፡፡ ልጆቻቸው ለደግ እናታቸው መጎናጸፊያ ሲሉ ከሞት ጋር አይን ለአይን ተፋጠዋል፤ በሞት
ሲረቱ እንኳ በቀኝ መዳፋቸው ጨብተው እንደያዙት አሊያም በደረታቸው ስር እንደሸሸጉት በክብር አንቀላፍተው ተገኝተዋል፡፡ ይህ መጎናጸፊያ
ለእመት የቢጫወርቅም ሆነ ለልጆቻቸው ከመለያ ምልክታቸውም በላይ ከእኛነታቸው ጋር የተጣባ የአንድነታቸው ፈትል ነው፡፡ መጎናጸፊያው
ከታቦተ-ጽዮንም በላይ ሀይልና ድል የሚያጎናጽፋቸው ታቦት ነው፡፡ መጎናጸፊያው ከቀስተ-ደመናም በላይ ህብራቸውና ውበታቸውም ነበር፡፡
ዛሬ፡-
የእናቱ ልጅ በአደባባይ እየዞረ በለፈፈው የሰላም መለከት ምክንያት
ወንድሞቹ በአንዳች ታምር ከየክፍላቸው ወጥተውና ከየስደታቸው ተመልሰው ከእናታቸው ቅዬ ተሰብስበዋል፡፡ የእናቱ ልጅ በመምጣታቸው
ተደስቶ ወንድሞቹን በናፍቆት እያቀፈ ስለ እናቱ መጎናጸፊያ ጉዳይ ሊያወጋቸው ሲጀምር ወንድሞቹ በቅጽበት ልጅነታቸው ገዝፎባቸው
“መሀረቤን ያያችሁ?” ለመጫወት በየአደባባዩ ክብ ሰርተው ተሰልፈው ይውሉ ጀመር፡፡ የእናታቸውን መጎናጸፊያ ትተው አንዳንዶች በሆዳቸው
ባደረ የቆየ የኩረፊያ ክር የጠለፉትን፣ሌሎች በልባቸው በከረመ የቂም ማግ የሸመኑትን፣ቀሪዎች በጥቅም ቀለም ያቀለሙትንና ዳር ዳሩን
በመለየት ክር ዘምዝመው የጠቀሙትን አይረቤ መሀረባቸውን ይዘው የእመት የቢጫወርቅ ቅዬን እየዞሩ መሀረቤን ያያችሁ? በማለት በከንቱ
ይውሉ ጀመር፡፡
ይህን ያስተዋለው የእናቱ ልጅ ልቡ በእልህ እንደተወጠረ ካንድ ትልቅ
ካብ እራስ ላይ ቆሞ እንዲህ በማለት ጮኸ፡- “የቱንም ያህል ወገንተኝነት የቱንም ያህል የዘር ናፍቆት ይዟችሁ ጨረቃ ላይ ብትወጡና
ከፍ ብትሉ ከወገናችሁ አንዱን እንኳን ወይም መንደራችሁን ፈጽሞ አትመለከቱም፡፡ ከጨረቃ ከፍታ ላይ የትኛውም በምድር ላይ ያለ ዘርና
ሀገር ተለይቶ አይታይም፡፡ ከፍታ ላይ ወጥታችሁ ቀና ብላችሁ ስታዩ የምትመለከቱት ምድርን ብቻ ነው፡፡ እናም ያኔ ኦ ምድር የምኖርባት
አፈር ብላችሁ መላው ምድርና የሰውን ልጅ ከማድነቅ በቀር ሌላ የጥበት ምርጫ አይኖራችሁም፡፡ ዝቅ ያለ ሰው ወይም የወረደ ሰው ብቻ
ነው ጥቃቅንን ነገር ሊታየው የሚችለው፡፡ ከፍ ስትሉ ትልቁን ነገር ብቻ ታስተውላላችሁ፡፡
ኑ የእውቀትና የንቃት መንኮራኮራችንን አስመጥቀን የአእምሯችን ጨረቃ
ላይ እንውጣ ያኔ ትልቋ ዋርካ ብቻ ተገልጣ እንያታላን፡፡ ያኔ የያዛችሁት ማህረብ እንደሆነ ትረዱና ገጣጥማችሁ መጎናጸፊያ ወይም
መቀነት ታሳክሉታላችሁ፡፡”
የእናቱ ልጅ ይጮኸል ጩኸቱ ግን በከንቱ አልነበረም፡፡ በክብ ተሰድረው
ያለ እድሜያቸው መሀረቤን ያያችሁ ከሚጫወቱት፣ ከሚያንቀላፉትና ከተኙት የነቁት፣ የተገለጠላቸውና የበራላቸው በልጠው ነበር፡፡


አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ